“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)
፩ ቆሮ ፯፥ ፳፭-ፍ፡ም ፤ ፪ ዮሐ፡ ም. ፩፥ ቍ. ፩-፮፤ ሐዋ. ፲፮፥ ቍ. ፲፫-፲፰፤ መዝ፡ ፵፬(፵፭)፥ ፱-፲። ማቴ ፳፭፥ ፩-፲፱ የዛሬ ምንባባት ሠርግ፣ ጋብቻ፣ ቤተሰብ የሚሉ ነጥቦች ተደጋግመው ይሰሙባቸዋል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጋብቻና ስለ ትዳር የለሽነት ይመክራል። ቅዱስ ዮሐንስ በፍቅር ኑሮ በሚገለጠው የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ የማመን ሐዋርያዊ እምነት ይጠቁማል። ከሐዋርያት ሥራ የተመረጠው ምንባባችንም ለቤተሰቧ ኹሉ ምክንያተ ድኅነት ስለኾነችው ስለልባሚቱ ሴት ስለልድያ ይተርካል። ምስባኩ “የንግሥት ልጆች ለክብርኽ ናቸው። ንግሥቲቱም ወርቅ ለብሳና ተጎናጽፋ በቀኝኽ ትቆማለች።” ብሎ ስለ ቤተሰባዊ የንጉሡ ክብር ቤተሰባዊ መልክ ምን እንደሚመስል ያሳየናል። ቅዱስ ማቴዎስም ጌታችን ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያትን በሠርግ መስሎ ሲያሰተምር አሰምቶናል። ሠርግ፣ ትዳር፣ ቤተሰብ። ይኽ ከእመቤታችን በዓለ ዕረፍት ወፍልሰት ጋር ምን ያገናኘዋል? እስኪ ወደ፣ ሠርግ እና ገቡ የሚሉትን ሦስት ቃሎች ከጌታችን ምሳሌ እንውሰድና ጉዳዩንም ራሳችንንም እንመልከተው። ወደ “ወደ” የሚለው ቃል እንቅስቃሴን ያመለክታል። “ወደ” የሚል ቃል ስንሰማ መድረሻውን እንጠብቃለን። ምናልባትም የሰውን ልጅ አጠቃላይ ምድራዊ ኑሮ ያመለክታል። የሰው ምድራዊ ኑሮ በአንድ ቃል ይጠቅለል ከተባለ “ወደ” ሳትገልጸው አትቀርም። ሲፈጠርም ወደ ተደርጎ ነው። የሰው ልጅ ተጓዥ ነው። ዋሻ ውስጥ እንኳ ዘግቶ ቢቀመጥ ከመጓዝ አያመልጥም። እርሱ ቢቆም እንኳ ጊዜ ተሸክሞት ይኼዳል። ወደደም ጠላም በዚኽ ምድር ላይ ሰው በማያቋርጥ ጉዞ ላይ ነው። እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሱ ድረስ እየኾነ ይኼዳል እንጂ ኾኖ አይቆምም። እየኾነ ነው። እየተጓዘ ነው። በአእምሮው ውስጥ የሚኖረው የተሳፈረበት የጊዜ ባቡር ይዞት