“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

፩ ቆሮ ፯፥ ፳፭-ፍ፡ም ፤ ፪ ዮሐ፡ ም. ፩፥ ቍ. ፩-፮፤ ሐዋ. ፲፮፥ ቍ. ፲፫-፲፰፤ መዝ፡ ፵፬(፵፭)፥  ፱-፲። ማቴ ፳፭፥ ፩-፲፱ 



የዛሬ ምንባባት ሠርግ፣ ጋብቻ፣ ቤተሰብ የሚሉ ነጥቦች ተደጋግመው ይሰሙባቸዋል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጋብቻና ስለ ትዳር የለሽነት ይመክራል። ቅዱስ ዮሐንስ በፍቅር ኑሮ በሚገለጠው የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ የማመን ሐዋርያዊ እምነት ይጠቁማል። ከሐዋርያት ሥራ የተመረጠው ምንባባችንም ለቤተሰቧ ኹሉ ምክንያተ ድኅነት ስለኾነችው ስለልባሚቱ ሴት ስለልድያ ይተርካል። ምስባኩ “የንግሥት ልጆች ለክብርኽ ናቸው። ንግሥቲቱም ወርቅ ለብሳና ተጎናጽፋ በቀኝኽ ትቆማለች።” ብሎ ስለ ቤተሰባዊ የንጉሡ ክብር ቤተሰባዊ መልክ ምን እንደሚመስል ያሳየናል። ቅዱስ ማቴዎስም ጌታችን ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያትን በሠርግ መስሎ ሲያሰተምር አሰምቶናል። ሠርግ፣ ትዳር፣ ቤተሰብ። ይኽ ከእመቤታችን በዓለ ዕረፍት ወፍልሰት ጋር ምን ያገናኘዋል? እስኪ ወደ፣ ሠርግ እና ገቡ የሚሉትን ሦስት ቃሎች ከጌታችን ምሳሌ እንውሰድና ጉዳዩንም ራሳችንንም እንመልከተው። 


  1. ወደ 

“ወደ” የሚለው ቃል እንቅስቃሴን ያመለክታል። “ወደ” የሚል ቃል ስንሰማ መድረሻውን እንጠብቃለን። ምናልባትም የሰውን ልጅ አጠቃላይ ምድራዊ ኑሮ ያመለክታል። የሰው ምድራዊ ኑሮ በአንድ ቃል ይጠቅለል ከተባለ “ወደ” ሳትገልጸው አትቀርም። ሲፈጠርም ወደ ተደርጎ ነው።  የሰው ልጅ ተጓዥ ነው። ዋሻ ውስጥ እንኳ ዘግቶ ቢቀመጥ ከመጓዝ አያመልጥም። እርሱ ቢቆም እንኳ ጊዜ ተሸክሞት ይኼዳል። ወደደም ጠላም በዚኽ ምድር ላይ ሰው በማያቋርጥ ጉዞ ላይ ነው። እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሱ ድረስ እየኾነ ይኼዳል እንጂ ኾኖ አይቆምም። እየኾነ ነው። እየተጓዘ ነው። በአእምሮው ውስጥ የሚኖረው የተሳፈረበት የጊዜ ባቡር ይዞት ይጓዛል። ለምን ይጓዛል ብለን መጠየቅ ብንችልም እንዲቆም ማድረግ ግን በፍጹም አይቻልም። እያንዳንዳችን እየኼድን ነው። በሌላ አባባል፣ የእኛ የሰው ልጆች ሌላው የወል ስማችን “ወደ” ነው። ወይዘሪት ወደ፣ አቶ ወደ፣ ቀሲስ ወደ፣ ወይዘሮ ወደ፣ አባ ወደ፣ ወዘተ. ኹላችን ወደዎች ነን። ይኽ መቀየር የማንችለው እውነት ነው። ስለዚኽ ለምን ወደ ኾንን ብለን አንዳንድ ሀብታሞች እንደሚያደርጉት በክራዮጄኒክስ ወደነታችንን ለማቆም መሞከር ሞኝነት ነው። ይልቅስ አስፈላጊው ጥያቄ የወደነቴ መድረሻ የት ነው? የሚል መኾን አለበት። ኑሮዬ እየኾኑ ማደር ከኾነ ኺደቱ በሞት ሲጠናቀቅ ምን ኾኜ እገኛለኹ? የሚል ቢኾን ጠቃሚ ይኾናል። ምክንያቱም ወደ አቅጣጫን ያመለክታል በአንድ ወይም በሌላ አቅጣጫ እየተጓዝን ነው። እየተጓዘ ያለ ሰው ሊጠይቀው የሚያስፈልገው ጥያቄ “የጉዞዬ ፍጻሜ በእውነት መድረስ የምፈልግበት ቦታ ነው?” የሚል ነው። ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ አንድ ወዳጁ ክርስቲያን መኾን ማለት ምን ማለት ነው? ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ ክርስቲያን መኾን ማለት እግዚአብሔርን መምሰል ማለት ነው ይላል። ስለዚኽ የክርስቲያን ወደነት ግቡ እግዚአብሔርን የሚመስል ሰው ኾኖ መገኘት ነው። ስለኾነም ክርስቲያን እያንዳንዷ ቀን ስታልፍ ዕለት ዕለት ራሱን እንዲኽ ሲል ይጠይቃል፦ “ዛሬ ወደነቴ ወዴት እየኼደ ነበር?” አቅጣጫውን ያስተካክላል። አቅጣጫውን የሚያስተካክለው ደግሞ ከተሰጠው የሠርግ ጥሪ አኳያ ነው። አቅጣጫዬ ወደ ሠርጉ ነው ወይስ ወደ ሌላ? የማንኛውም ሰው ኑሮ መልክ ይኽን ጥያቄ በመጠየቅና ባለመጠየቅ ላይ ይወሰናል። ብዙ ሰዎች ይኽን ጥያቄ መጠየቅ እንዳለባቸው እንኳን አያስተውሉም። 

       

  1. ሠርግ 

ሠርግ ቤት የተዛምዶ ቦታ ነው። ሙሽሪት ከሙሽራዋ፣ የሙሽራው ቤተሰቦች ከሙሽሪት ቤተሰቦች ይዛመዱበታል። ከጥብቅ ዝምድናቸው የተነሣም ኹሉም በአንድ ቃል ሠርገኞች ተብለው ይጠራሉ። ሙሽራው በሙሽሪቱ መገኘት ሙሽራ ይባላል። ሙሽሪትም ሙሽራዋ ስላለ ሙሽሪት ትባላለች። እንደ ጥልፍ፣ እንደጉንጉን አበባ የተዋሐደ አንድነታቸውም ውብ ነውና የተጌጠ፣ የተጎነጎነ ሠርግ ይባላል (ደስታ ተክለ ወልድ፣ “ሠረገ፣ ሰረገ”ን፤ ዕብራይስጥ B-D-B, שָׂרַג ተመልከት)። ሠርጉ፣ ውሕደቱ የሙሽሮቹ ቢኾንም በሙሽሮቹ ውስጥ የሙሽሮቹ የኾኑት ኹሉ ይዋሐዳሉ። ኹለት ቤተሰብ የነበሩት በሙሽሪትና በሙሽራው ትሥሥር አንድ ሥጋ ይኾናሉ። መንግሥተ ሰማያትም እንዲኽ ናት። ሰውና እግዚአብሔር፣ ፍጥረትና ፈጣሪ አንድ የሚኾኑባት እውነት ናት። ሞት የሚባል ብቸኝነት፣ ኃጢኣት የሚባል ዘመድ ማጣት የሌለባት ሠርግ ናት። በራሷ ሕይወት የሌላት ፍጥረት የእግዚአብሔርን ሕይወት እንደወርቀዘቦ ሸማ ለብሳና ተጎናጽፋ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ክብር ወርሳ የምትገለጥበት ዝምድና ናት። የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ኾኖ ይኽን ጥሪ አሰምቶናል። የትዳሩን ብርታት እስከመቃብር ድረስ አብሮን ወርዶ አሳይቶናል። እኛም ድምፁን ሰምተን ዮርዳኖስ ወርደን ጥምቀቱን ተካፍለን፣ ቅዱስ ሜሮን ተቀብተን ለእርሱ ብቻ ልንኖር ታትመንለት ተከትለነዋል። ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ትዳር ቢኖረንም ባይኖረንም፣ ልጆች ቢኖሩንም ባይኖሩንም፣ ሀብት ቢኖረንም ባይኖረንም በኹሉ ውስጥ እርሱን እናመልካለን እንጂ ጎደለን ብለን አናማርርም፤ ተረፈን ብለን አንቀናጣም። ምክንያቱም፣ እኛ ወደ ሠርግ ቤት እየኼድን ነው። ከፊታችን የተዘጋጀልንን የደመቀ ሠርግ ትተን መንገድ ላይ በተሰጡን ወይም ባልተሰጡን ነገሮች ላይ ሐሳባችን አይባክንም። የተሰጠን በጸጋ ለሌሎች እንድናካፍለው፣ ያልተሰጠንም በፍቅሩ ብዛት እንደኾነ ስለምናውቅ የመጣና የኼደው የዜና ወሬ ልባችንን አያባትተውም። በምሥጋና ቢስነት የሚባክን የሕይወት ሽራፊ የለንም። 


  1. ገቡ        

እንደ ልድያ ቃሉን የሚሰሙ፣ የልባቸውን ድንግልና ለዚኽ ዓለም ገዢ ያላስረከቡ ቅዱሳን ወደ ሠርጉ ይደርሳሉ። ሙሽራውን ያገኛሉ። ከእርሱም ጋር ወደ ሠርጉ ይገባሉ። እነርሱ እርሱን መስለው ይጠብቁታል፤ መልካቸው እርሱን ስለሚመስሉም ሲያያቸው ያውቃቸዋል፤ “በጎቼን ዐውቃቸዋለኹ፤ እነርሱም ያውቁኛል” እንዲል (ዮሐ 10፣ 14)። ይኽን መድረሻችንን እንድናስተውልም፣ በጸጋና በምሥጢር እንድንሳተፍ ነው በየዓመቱ ፍልሰታን የምናከብረው። ዓይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ በሰው ልቡናም ያልታሰበው እግዚአብሔር ለምትወድደው ለቤተ ክርስቲያኑ ያዘጋጀውን፣ የአንድ ልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በሥጋ በነፍስ ወርሶ የመኖር ጸጋ የቤተ ክርስቲያን አባል፣ የቤተ ክርስቲያን እናትና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የኾነችው ምልዕተ ጸጋ ድንግል ማርያም በዕረፍቷ፣ በፍልሰቷ በሥጋም በነፍስም ወርሳዋለች። ድንግል በፍልሰቷ የወረሰችውን በደብረ ታቦር የተገለጠውን ለሰው ልጅ የተዘጋጀ መለኮታዊ ክብር እናደንቃለን፤ እንደሰትማለን። ወደ በጉ ሠርግ መግባት ምን እንደሚመስል እናውቃለን፤ ከእኛ አንዲቱ የኾነችው ድንግል ማርያም ያለ አንዳች ስስት ለእግዚአብሔር የሰጠችው ምድራዊ የመከራ ኑሮዋ ሲጠናቀቅ ሞት ወደሌለበት የበጉ ሠርግ እንደገባች፣ እግዚአብሔር ለሚወድዱት ኹሉ ያዘጋጀውን የልጁን ትንሣኤ እንደወረሰች በእምነት አይተናልና። ከዚኽም በላይ፣ በቅዳሴ ከዚኽ የበጉ ሠርግ በእምነትና በተስፋ እንሳተፋለን። የታረደውን የእግዚአብሔር በግ ሥጋውን በልተን፣ ደሙን ጠጥተን ደስ ይለናል። ሥጋውን ሥጋችን ደሙን ደማችን አድርጎልን፣ ቅዱስ መንፈሱን ሞልቶን እርሱ ብቻ በእኛ እንዲኖር ራሳችንን “አሜን!” ብለን በደስታ እንሰጠዋለን። አዎን በምሥጢረ ቁርባን እርሱ ወደ እኛ ይገባል፤ እኛም ወደ እርሱ እንገባለን። ከብልኆቹ ደናግል ጋር የንስሐ ዘይታችንን፣ የምግባር መብራታችንን ይዘን ወደ ሠርጉ እንገባለን። ወደነታችን በበግነት ተፈጽሞ፣ ክብሩን ወርሰን፣ ጸጋውን ተጎናጽፈን ከእመቤታችን ጋር በንጉሡ ቀኝ እንቆማለን። 


ወደ እርሱ እንድንደርስ የፈጠረን፣ በአንድ ልጁ የመስቀል ሠርግ ወደራሱ ያቀረበን፣ በቅዱስ መንፈሱም ቤተ ክርስቲያንን ለአንድያ ልጁ የዳረ ልዑል እግዚአብሔር አብ ዛሬም ዘወትርም ምሥጋና ይግባው። አሜን።       


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”