“ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል።”
፪ኛ፡ ቆሮ፡ ም. ፱፥ቍ. ፮-ፍ፡ም፤ ያዕ፡ ም. ፫፥ቍ. ፲፫-ፍ፡ም፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፳፯፥ቍ. ፳-፳፮፤ ማቴዎስ፡ ም. ፲፫፥ ቍ. ፲፰-፳፬
ከሠኔ 25 እስከ መስከረም 25 ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት ይባላል። የዛሬ ምንባቦችም ክረምት፣፣ ዘር መዝራት፣ ፍሬ መስጠት የሚሉ ጭብጦችን ያነሣሉ። መዝሙረኛው እግዚአብሔርን “ለእንስሳት ሣርን የሚያበቅል፣ የሰውንም እርሻ በልምላሜና በፍሬ ባርኮ የሚመግብ እንደኾነ እያነሣ እግዚአብሔርን በመጋቢነቱ ያመሰግናል። ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ምእመናን ሀብቱን ለድኾችና ለችግረኞች የቤተ ክርስቲያን አባላት የዘራ ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ዕጥፍ ድርብ በረከት እንደሚቀበል እየነገረ የልግስናን ገበሬዎች ያበረታታል። ቅዱስ ያዕቆብም ሰው በልቡ ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥበብ ቢዘራ ንጽሕና፣ ዕርቅ፣ ገርነት፣ ትሕትናን፣ ምሕረትን እንደሚያበቅል ይናገራል። ሰው በልቡ ውስጥ የአጋንንትን ጥበብ ቢዘራ ደግሞ ቅንዓት፣ አድመኛነት፣ ሑከት፣ ክፉ ሥራ ሁሉ እንደሚበቅሉበት በግልጽ ያስተምራል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩት ፍሬዎች የትኞቹ ናቸው? በአጥቢያችን የሚታዩት ፍሬዎችስ የትኞቹ ናቸው? በእኔ ሕይወት ውስጥ የሚታዩት ፍሬዎችስ? ከአንደበታችን የሚወጣው፣ ከአኗኗራችን የሚንጠባጠበው ፍሬ በልባችን ውስጥ የማንን ጥበብ ዘርተን እንደምንኖር ይመሰክርል/ብናል። የሐዋርያት ሥራ ምንባብ ደግሞ በልቡ የእግዚአብሔር ጥበብ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የዘራው ገበሬ ቅዱስ ጳውሎስ በእሥረኝነት ኾኖ አሣሪዎቹን ሲያጽናና ያሳየናል። የወንጌል ምንባባችንም ጌታ ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያብራራላቸው እንመለከታለን። በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ይኽን ማብራሪያውን የሚጀምረው ግን ዛሬ ከተነበበው ክፍል ጥቂት ከፍ ብሎ ነው። እንዲኽ ይላል፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል።… ላለው ይሰጠዋልና፤ ይበዛለትማል። ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” (ማቴ 13፣ 11)። ጌታ ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ ለደቀ መዛሙርቱ የሚያብራራላቸው ለዚኽ ነው። እነርሱ የሰሙትን አልረሱም፤ አልዘነጉም። ባይገባቸውም ቀረብ ብለው ጠየቁ እንጂ “የሚያወራው ነገር አይገባኝም!” ብለው የሚገባቸው ሌላ ቀለል ያለ ነገር ፍለጋ አልኼዱም። ቀረብ ብለው ጠየቁት እንጂ። ስለጠየቁም ባይገባቸውም ያልዘነጓት ምሥጢር ተብራራችላቸው። ልባቸው የበረረ ወፍ ኹሉ የሚያርፍበት መንገድ አልነበረም። ስለዚኽም፣ ቀረብ ብለው ጠየቁ። እንግዲኽ የሐዋርያትን ዕድል ፈንታ ያድለን ዘንድ ስለሐዋርያት የምንማልድ እኛ እንደእነርሱ መልካሙን ዘር እንደመልካም ዐፈር እንድንይዝ ምን እናድርግ? ሦስት ነገሮች እጅግ አስፈላጊ ኾነው ይታዩኛል።
ጊዜ መስጠት
ሐዋርያት ጌታ ኢየሱስ “መስማት የሚችል ጆሮ ያለው ይስማ!” በሚል ማሳሰቢያ አጅቦ የተናገረውን ቃል እንዲያው ሰምተው አላሳለፉትም። ጊዜ ሰጡት። የእግዚአብሔርን ቃል በጽሙና ማድመጥ በቤተ ክርስቲያናችን እጅግ የተተወ ሥራ ነው ብዬ አምናለኹ። ለዜማ የሰጠነው ትኩረት ቃሉን በቅጡ እንዳናነብብ አድርጎናል። ቅዳሴ ላይ እንኳ ቃለ እግዚአብሔር በቅጡ የሚነበብባቸው አጥቢያዎች ማግኘት ብርቅ ነው። አንባቢው አንብቦ ሳይጨርስ በላዩ ላይ ተሰጥዎ ማዜም ልማድ ኾኗል። ጉዳዩን በግለሰብ ደረጃ ካየነው የባሰ ነው። ኦርቶዶክሳውያን መጽሐፍ ቅዱስን ይሳለሙታል እንጂ ለቅዱስ ቃሉ የጽሙና ጊዜ ሰጥተው ቃሉ በልባቸው ውስጥ እንዲዘራ በጽሙና ጊዜ አይሰጡትም። ስለዚኽም፣ የቃሉ ዘር በልባቸው ውስጥ የለም። እነሆ! ቤታችን በእንክርዳድ ተሞላ። ኑሯችን የክርስቶስ መዓዛ የራቀው፣ ንግግር ምግባራችን ከማያምኑ አሕዛብ የማይሻል ኾነ። ኪርዬ ኤሌይሶን!
በቤተ ክርስቲያንነት ማንበብ
ለቅዱስ ቃሉ ጊዜ የምንሰጠው የሙሽራችን ቃል ስለኾነ ነው። ቅዱስ ቃሉን እና እንደመንገደኛ አናንብበውም። የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ለእኛ ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቶናልና። ቅዱስ ቃሉ የሙሽራችን፣ የወዳጃችን፣ የሕይወታችን ቃል ነው። ስለዚኽም በቤተ ክርስቲያንነት፣ በቤተ ክርስቲያን አእምሮ፣ በኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ጥበብ እናነብበዋለን። እንጂ ከንቱ ጥያቄዎችን አንጠይቅም። ቅዱስ ቃሉን ጊዜ ሰጥተን በቤተ ክርስቲያንነት ስናደምጥ በምሥጢረ ጥምቀት የለበስነውን፣ በምሥጢረ ሜሮን የታተምንበት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእኛላይ እንዲሠራ ዕድል ያገኛል። ቤተ ክርስቲያንን በጸጋው ሞልቶ የሚኖረው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ያበራዋል፤ ይከፍተዋል። የጌታ ኢየሱስን ጥዑም ድምፁን ስለሚያሰማን ሌላ ድምፅ አያማልለንም። ጣፋጭ ድምፁን እየሰማን መስቀላችንን ተሸክመን እንከተለዋለን። በትንሣኤው እርሱን ለመምሰል በሞቱ እርሱን ለመምሰል እንመኛለን (ፊልጵስዩስ 3፣ 11)። ለቅዱስ ቃሉ ጊዜ ስንሰጥ፣ የሙሽራዋን ቃል የምትናፍቅ ቤተ ክርስቲያንነታችንን እንኖራለን። የሐዘናችን ምንጭ የኾነው ኃጢኣትና ኃጢኣተኝነት ከእኛ በቅዱስ ቃሉ ኃይል ይርቅልናል። ኅሊናችን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል። በቤተ ክርስቲያንነታችን የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶናልና አእምሯችን በእግዚአብሔር ሰላም ያርፋል።
በቅዱስ ቍርባን ማንበብ
ባለራእዩ ዮሐንስ ማኅተሙን የፈታው የታረደው በግ ነው (ራእይ 5)። ቅዱስ ሄሬኔዎስ የሚባል ከ1800 ዓመታት ገደማ በፊ የነበረ አባት “የእኛ ትምህርታችን ከቍርባናችን ጋር ቍርባናችንም ከትምህርታችን ጋር አንድ ነው” ይላል። ክርስቲያን እኔ የእኔ ለእኔ የሚለውን የኃጢኣት ኑሮ በጥምቀት ከእርሱ ስላስወገደ ለክርስቶስም ብቻ ይኾን ዘንድ ስለታተመ ኑሮው ኹሉ በቅዱስ ቍርባን አብሮት ለሚኖረው ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። የዕውቀት ጥግ፣ የጥበብም ኹሉ ፍጻሜ ኾኖ የሚያውቀው ጌታ ኢየሱስን ብቻ ስለኾነ ከቅዱስ ቍርባን ውጪ የኑሮ ጥበብ፣ የሕይወት ፍልስፍና የለውም። የዘሪውን ቅዱስ ቃል ስንሰማ የመገለጥ ኹሉ ፍጻሜ በኾነው በቅዱስ ቍርባን በኩል ያነብበዋል። ቃሉን ማድመጡ ወደ ቅዱስ ቍርባን አንድነት ይመራዋል። በቅዱስ ቍርባን ከእግዚአብሔርና ከወንድሞችና እኅቶቹ ጋር የሚኖረን ቍርባናዊ አንድነት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ከትናንት የበለጠ እንዲያደምጥ፣ እንዲረዳ፣ ቃሉ በውስጡ እንዲኖርና ፍሬውም በኑሮው እንዲገለጥ ያስችለዋል። ሙሽርነቱን በጽሙና ያስተዋለ ሙሽራውን ጌታ ኢየሱስን ይከተላል፤ ሠላሣ፣ ስድሳ፣ መቶ ያማረ ፍሬ ያፈራል።
አንድ በመካከለኛው ዘመን የነበረ በቅዱስ ቃሉ ሕይወቱ እንዲበራለት ይመኝ የነበረ ሰው እንዲኽ እያለ ይጸልይ እንደነበረ ይነገራል፦
አቤቱ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ!
የልቤን ጨለማ አብራልኝ።
ትእዛዝኽን ሰምቼ እፈጽም ዘንድ
ታማኝ እምነትን ፣
እርግጠኛ ተስፋን፣
ፍጹም ፍቅርን፣
ማስተዋልና ዕውቀትን
በምሕረትኽ ስጠኝ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ