ትንሣኤ ስም እና ቅድስና

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን!

በአማን ተንሥአ!

የዕለቱ ምንባቦች፦ ፩ኛ፡ ቆሮ፡ ም. ፲፭፥ ቊ. ፩-፳፤ ፩ኛ፡ ዮሐ፡ ም. ፩፥ቊ. ፩-ፍ፡ም፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፳፫፥ ቊ. ፩-፲፤ ዮሐንስ፡ ም. ፳፥ቊ. ፲፱-ፍ፡ም፤ ዮሐንስ፡ ም. ፲፯፥ ቍ. ፩-ፍ፡ም።


  1. ትንሣኤ 

የበዓላት ኹሉ በኵር፣ የቤተክርስቲያን ትርጉምና ድሏ የሙሽራዋ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው። ስለዚኽም፣ ከበዓላት ኹሉ ከፍ አድርጋ ትንሣኤን ታከብራለች። በክርስቶስ ትንሣኤ ውስጥ ያለውን ደስታ፣ ተስፋና ሕይወት በሚገባ እንድናጣጥመውም ስምንት ቀናትን እንደ አንድ ቀን ቆጥራ ስታከብር፣ እርሱም አልበቃ ብሎ እስከ ዕርገት በዓል ድረስ ያሉትን 40 ቀናት ስትጨምርበት እናያታለን። ለምን? ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት ካልኾነ ቤተክርስቲያን ከንቱ ናት። የነቢያት ትንቢት፣ የሐዋርያትም ስብከት፣ የሰማዕታት መከራ፣ የእናንተም ጾምና ጸሎት የመቃብር ድንጋይ ደፍጥጦ በዜሮ የሚያባዛው ከንቱነት ይኾናል። ሰው ኾኖ መኖርም ትርጉም የሌለው የመከራ ቀንበር ይኾናል። ግን ክርስቶስ በእውነት ከሙታን ተነሥቷል ስለዚኽም ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው፣ “በኹሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ኹልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።” (2ኛ ቆሮ. 4፡8) ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይለናል! (ፊል 4፡4)     

  1. ስም

ይኽ ዛሬ ከዮሐንስ ወንጌል የተነበበው ምንባብ የጌታ ኢየሱስ የሊቀ ካህንነቱ (כהן גדול) (ἀρχιερεύς) ጸሎት ይባላል። ከዚኽ ጸሎት ቀጥሎ የሚመጣው የዓለሙን ኃጢኣት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ የተቀበለው መከራ ነው። በዚኽ ጸሎት ጌታ ኢየሱስ በእርሱ ላይ የሚደርሰውን መከራ ወደ ሥርዓተ መሥዋዕት ይቀይረዋል። ጌታ ኢየሱስ በዚኽ የዐቢይ ካህንነቱ  ጸሎት ውስጥ “አባት ሆይ፣… እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኹኽ” ሲል እንሰማዋለን። የሰጠው ሥራ ምንድን ነበረ? ጥቂት ዝቅ ብለን ስናነብ “ስምኽን ገለጥኹላቸው” ይለናል። በቀላል አማርኛ “አንተን አስተዋወቅኋቸው፤ አንተን እንዲያውቁ አደርግኋቸው” ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ስም ማወቅ ማለት ስለ እግዚአብሔር መረጃ መሰብሰብ ማለት ሳይኾን እግዚአብሔርን በእርሱነቱ መተዋወቅ፣ ከእርሱ ጋር ግንኙነት መመሥረት ማለት ነው። ብቻው እውነተኛ አምላክ የኾነው እርሱንና የላከውን አንድ ልጁን ማወቅ የዘለዓለም ሕይወት የኾነውም ለዚኽ ነው (ዮሐ. 16፡ 3)። ሕይወት የሚፈልግ ይምጣ! ቃሉ የኾነውን ልጁን ይስማ። በቅዱስ ቁርባን አብሮን የሚኖረውን ልጁን ይቀበል። እግዚአብሔርን ይወቅ። ከእግዚአብሔር ጋር ይተዋወቅ። ልጁ ያለው ሕይወት አለው። ልጁ የሌለው ሕይወት የለውም፤ ያለ እግዚአብሔር መኖር “እየሞቱ ማደር” እንጂ ሕያውነት አይባልምና። የጥንት ክርስቲያኖች በትንሣኤ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ልጅ በቅዱስ ቁርባን ተቀብለው  በእግዚአብሔር አብ ሕይወት፣ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚኖሩ ሲያመለክቱ ራሳቸውን “ሕያዋን” οἱ ζῶντες ብለው ይጠሩ ነበረ።  እርስዎ ሕያው ነዎት? 

  1. ቅድስና       

በጌታ ኢየሱስ የዐቢይ ካህንነቱ ጸሎት ውስጥ ከሰማናቸው ነጥቦች አንዱ መቀደስ የሚል ነው። ጌታ ኢየሱስ “ቅዱስ አባት ሆይ!... በእውነትኽ ቀድሳቸው።… በእውነት የተቀደሱ እንዲኾኑ እኔ ደግሞ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለኹ።” ሲል እንሰማዋለን። ምን ማለት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ቅድስና የእግዚአብሔር ብቻ የኾነ ነገር ነው። ቅዱስ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሌሎች ኹሉ ቅዱስ የሚባሉት ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት መሠረት ነው። ቅዱስ ማለት ልዩ ነውና ፍጹም ልዩ የኾነው እርሱ ብቻ ስለኾነ። ፍጡራን ቅዱሳን ሲባሉ ከቅዱሱ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት መሥርተዋል፤ ለእግዚአብሔር ተለይተዋል ማለት ነው። ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ናቸው። በሌላ አባባል፣ መሥዋዕት ናቸው። ጌታ ኢየሱስ “በእውነት የተቀደሱ እንዲኾኑ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለኹ” የሚለውን ምንባብ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲያብራራ “ራሴን መሥዋዕት አድርጌ አቀርባለኹ ማለት ነው” ይላል፤ መቀደስ መሥዋዕት መኾን መቀደስም ራስን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ነውና። እንግዲኽ የተጠመቅነው፣ በምሥጢረ ሜሮንም በመንፈስ ቅዱስ ተለይተን (ተቀድሰን) የታተምነው ይኽን የዐቢይ ካህናችንን የመሢሑ ኢየሱስን ቅዱስ ሕይወት እንካፈል ዘንድ ነው። ራሳችን የኾነው እርሱ ራሱን በአባቱ ፊት ለእኛ ቀድሷልና አካሉ የኾንን እኛ ደግሞ ራሳችንን ለእርሱ እንቀድስ ዘንድ ግድ ይለናል። ስሜ ይቀደስ ሳይኾን ስምኽ ይቀደስ! መንግሥቴ ትምጣ ሳይኾን መንግሥትኽ ትምጣ! ፈቃዴ ትኹን ሳይኾን ፈቃድኽ ይኹን! ብለን ዕለት ዕለት ለኃጢኣት እየሞትን ራሳችንን ለኃጢኣት ከሞተው ከክርስቶስ ጋር አንድ ስናደርግ አንድ ልጁን ከሞት ያስነሣው የእግዚአብሔር አብ ፍቅር በእኛ ላይ ይገለጣል። በመንፈስ ቅዱስም የልጁን ትንሣኤ ያለብሰናል፤ ሕያውነቱን ወርሰን ሕያዋን እንኾናለን። 


ራሱን ለእኛ ቀድሶ ከአባቱ ጋር አንድ ያደረገን አንድያ ልጁን የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል 

በቤተ ክርስቲያን ክብር ምሥጋና ይኹንለት። አሜን። 


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”