“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)
የዕውቀት ድንበር፣ ከላይ መወለድና የፍቅር ነጻነት
ምንባባት፦ ሮሜ 7፡1-19፤ 1ኛ ዮሐ 4፡ 18-ፍጻሜ፤ ሐዋ 5፡ 34-ፍጻሜ፤ መዝ 16(17)፣ 3፤ ዮሐ 3፡ 1-20።
ዐቢይ ጾም ከተጀመረ ሰባተኛ ሳምንት ላይ ደረስን። ይኽ ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል። ቤተ ክርስቲያን ኒቆዲሞስ ለተሰኘው በጌታ መዋዕለ ሥጋዌ ለነበረ መምህር የተሰጠውን ምሥጢረ ጥምቀትን የሚመለከት ትምህርት እያስታወሰች፣ ደግሞም ኒቆዲሞስ ሲጀምር በጨለማ ቢመጣም ኋላ ላይ ጌታን አምኖ ያደረገውን በጎ ምግባር እየዘከረች በጾመ ድጓዋ ሙሽራዋን በኒቆዲሞስ አንደበት “ረቢ ንብለከ፤ ነአምን ብከ” (መምህር እንልኻለን፤ እናምንብኻለንም) እያለች ትዘምራለች። በጥንቱ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ዐቢይ ጾም ንዑሰ ክርስቲያን በፋሲካ ሌሊት ለሚካኼደው ጥምቀታቸው የሚዘጋጁበት ጊዜ ነበረ። ስለዚኽ የጥምቀት ጊዜያቸው ከመድረሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ይኽን ምሥጢረ የሚመለከት ትምህርት መማራቸው የሚገባ ነው። ከእነዚኽ ምንባቦች ውስጥ ሦስት ነጥቦችን እናንሳና ራሳችንን እንመልከት።
የዕውቀት ድንበር
ዛሬ በምንባቦቹ ውስጥ ያገኘናቸው ኒቆዲሞስና ገማልያል የሚባሉ መምህራን በማመንና ባለማመን ድንበር ላይ ቆመው እናገኛቸዋለን። የሚያዩትን ጌታ ኢየሱስ የሚባል እውነት፣ በትምህርት ከሚያውቁትና ይኾናል ብለው ከሚጠብቁት ለማስማማት የቸገራቸው ይመስላል። ገማልያልም የሐዋርያትን ስብከት ለተቃወመው የአይሁድ ሸንጎ “ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋል፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፏቸው ዘንድ አይቻላችኹም” ብሎ ያሳስባል። “እንደኾነ”ን ከሥሯ እናሥምርባት። ኒቆዲሞስ ደግሞ ሰው በማያይበት፣ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ “መምህር ኾነኽ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣኽ እናውቃለን” ብሎ ዕውቀቱን ይገልጣል። ኹለቱም መምህራን በዓይናቸው ፊት እየተከናወነ ያለውን ነገር አስተውለዋል። ዕውቀታቸው በፈቀደላቸው መጠንም ገምግመዋል። ዐዲስ እውነታ ከፊታቸው ቆሟል። ይኽን እውነታ እንዳልተፈጠረ ማለፍ አልቻሉም። ግን ለእውነታው ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለመስጠት ገና ድርድር ላይ ናቸው። የማስተዋል ዐቅማቸውን በመጠቀም ከአለማመን ጨለማ ለመውጣት ድንበሩ ላይ ደርሰዋል። በብርሃን ወደተመላው የማመን ዓለም ሊገቡ ጫፍ ላይ ናቸው። ግን ገና አልተሻገሩም። የሰው ሥራ፣ የሰው ትምህርት፣ የሰው ሐሳብ፣ የሰው ባህል፣ የሰው ዕቅድ፣ ወዘተ. የሚባሉ ነገሮች እግሮቻቸውን ይዘዋቸዋል። ጌታ ኢየሱስን እንደጴጥሮስ “አንተ የእግዚአብሔር መሢሕ ነኽ” ሲሉ አንሰማቸውም። ይልቁንም፣ “መምህር” “የእግዚአብሔር ሥራ” የሚሉ ደብዛዛ አገላለጾችን ይጠቀማሉ። Strategic ambiguity ልንለው እንችላለን።
ምክንያቱም፣ ኒቆዲሞስም ኾነ ገማልያል የኢየሱስን መሢሕነት ከተቀበሉ፣ ክብራቸውን፣ ምቾታቸውን፣ ኑሯቸውን ጥለው እርሱን መከተል እንደሚኖርባቸው ያውቃሉ። መምህራን ናቸውና መሢሑ የእግዚአብሔርን መንግሥት ያመጣልና እርሱ መጥቶ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር ማሰብ በሕይወትና በሞት መካከል ያለውን ልዩነት ያለማወቅ እንደኾነ ያውቃሉ። መሢሑ የጥያቄ ኹሉ መልስ ነውና እርሱ ሲመጣ ኹሉን ትቶ መከተል እንደሚገባ ተምረዋል።
ይኽ ኢየሱስ የሚባል ገሊላዊ መምህር አንደበቱ ጥዑም፣ ትምህርቱም ግሩም ናት። ደግሞም አንዳንድ ጊዜ ታላላቅ ምልክቶችን ያደርጋል። ግን ለራሱ ማረፊያ አንዲት ታዛ እንኳ የለችውም። በዙሪያውም ያሉት አብዛኞቹ እዚኽ ግባ የሚባል ማኅበራዊ ስፍራ ያላቸው አይደሉም። ዓሣ አጥማጆች፣ ቀራጮች፣ ከሕመም የተፈወሱ ሴቶች፣ ወዘተ. ናቸው። እርሱን መሢሑን ብዬ ከተቀበልኹ ፈቃዴን ለፈቃዱ ላስገዛ ነው፤ ወንድሞቼ እኅቶቼ የሚላቸውን የተናቁትን፣ ደካሞችን፣ ኃጢኣተኞችን እጆቼን ዘርግቼ ልቀበል ነው። እስራኤላዊ መኾን፣ ፈሪሳዊ መኾን፣ ሕግ ጠባቂ መኾን፣ ገንዘብ ማዋጣት፣ በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ መጓዝ፣ መገረዝ፣ ወዘተ. አይበቃም። ኹሉን ትቶ እርሱን መከተል ይጠይቃል። ስንት ዓመት ሙሉ የገነባኹት ስሜስ? ክብሬስ? ቤቴስ? ንብረቴስ? ትዳሬስ? ማኅበራዊ ኑሮዬስ? ክብሬስ? (ልክ አብዛኛው የእኛ ሰው ቅዱስ ቁርባን ላይ ያለውን “አልበቃኹም” የሚባለውን አመለካከት ይመስላል። አይደል?)
እንዲኽ ያለው በማመንና ባለማመን መካከል መዋለል የሚወለደው ሥጋ ለብሶ የተገለጠውን በቅዱስ ቁርባንም አብሮን የሚኖረውን የእግዚአብሔር መንግሥት ማየት፣ መቅመስ፣ መዓዛውን ማሽተት ካለመቻል ነው። ለምን? ይኽን ለማድረግ ከላይ መወለድ (በድጋሚ መወለድ) ይጠይቃል።
ከላይ መወለድ
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጥቶ ስለመምህርነቱ ሊመሰክር ሲሞክር ጌታ ኢየሱስ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። በአማርኛውና በግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ዳግመኛ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ἄνωθεν የሚል ነው። ይኽ ቃል ዳግመኛ ወይም ከላይ የሚሉ ኹለት ትርጉሞች አሉት። አንደኛው ፍቺ ሌላኛውን ፍቺ ያብራራዋል። ጌታችን “ዳግመኛ ካልተወለደ” የሚለው ልደት ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የኾነ ልደት ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማየት አይችልም። ከእግዚአብሔር መወለድ ማለት ምን ማለት ነው? ከእግዚአብሔር መወለድ ልጅ ራሱን በወላጆቹ ላይ እንደሚጥል ራስን በእግዚአብሔር ላይ ሙሉበሙሉ ጥሎ መኖር ነው። እግዚአብሔርን በአባትነቱ ሳይጠራጠሩ መቀበል ነው። የራስን ሕይወት ለማቆም የሚደረግ መውተርተርን ትቶ፣ ከክብር ፍለጋ፣ ከዝና ጥማት፣ ራስን ለማኖር ከሚደረግ መፍተርተር ራስን ባዶ አድርጎ፣ እያንዳንዷን ቅጽበት ከእግዚአብሔር ለጋስ እጆች እየተቀበሉ መኖር ነው። ልጅን በወላጆቹ ፊት የሚያቆመው የወላጆቹ ፍቅር ብቻ እንደኾነ እንዲኹ በእግዚአብሔር ፊት ፍቅሩን ብቻ ተማምኖ መኖር ፍቅሩን እየተነፈሱ መኖር። እኔ ለእኔ የእኔ የሚለውን መንፈስ በውኃ ጥምቀት ቀብሮ፣ የክርስቶስን መንፈስ ተቀብሎ በመንፈስ መኖር ነው። ራስን ባዶ በማድረግ በነጻነት መኖር!
የፍቅር ነጻነት
ሰው ይኽን ራስን ባዶ አድርጎ የመኖርን መንገድ በመቀበል በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ሲሞት “ክርስቲያን ኾነ፤ የክርስቶስ አካል ኾነ፤ ነጻ ወጣ!” ይባላል። የኑሮው መስፈሪያም በምሥጢረ ሜሮን የተቀበለውን ቅዱስ መንፈስ ምሪት እንጂ የማኅበረሰብ መለኪያ (societal standard) አይደለም። በጎውን በጎ ክፉውን ክፉ የሚልበት ሚዛኑ የእግዚአብሔር ሐሳብ እንጂ ሰዎች ተስማምተው የፈጠሩት ልኬት አይደለም። ስለዚኽም ማኅበረሰብ ሲያብድ አያብድም፤ ተስፋ ሲቆርጥ አብሮ ተስፋ አይቆርጥም፤ በደስታ ሲሰክርም ደስታው ከእግዚአብሔር መኾኑን በጽሙና ያስተውላል። ክርስቲያን ነጻ ሰው ነው። ነገን በመፍራት ላይ ከተመሠረተው የዓለም አኗኗር ነጻ ነው። በልግስና ስለሚኖር ሲጦዝ በመገዳደል፣ ሲረግብ በመዘራረፍ ከሚኖረው ኋላ ቀር የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ነጻ ነው። ነገ አያስፈራውም። “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚኽ፣ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” (መዝ. 45(46)፡ 1)። (God is our refuge and strength, an ever present help in trouble. Therefore will not we fear, though the earth be removed, and though the mountains be carried into the midst of the sea)
እያንዷንዷ የሕይወቱ ሽራፊ ከወደደው ከእግዚአብሔር የምትለገስ ስጦታ እንጂ እርሱ በጥበቃው፣ በሀብው፣ በጉልበቱ፣ በሥራው፣ ወዘተ. የሚፈጥራት፣ የሚያረዝማት አለመኾኗ ይገባዋል። ስለዚኽ፣ ራሴን ማኖር አለብኝ ከሚል ከመቃብር ድንጋይ ከማያሳልፍ ከንቱ ጭንቀት ነጻ ኾኖ ይኖራል። በምሥጢረ ሜሮን የተቀበለውና የሚመራው የፍቅር መንፈስ ወንድሙን እንዲወድድ ያስችለዋልና አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትመኝ፣ በሐሰት አትመስክር፣ ወዘተ. የምትለው የሙሴ ሕግም አትፈርድበትም። ክርስቲያን የሚኖረው በእግዚአብሔር መንግሥት፣ የበጉ ሠርግ በኾነው በሥርዓተ ቅዳሴ ውስጥ ነው። ይኽ መንግሥት በፍጥረቱ ተገልጦ፣ በምሥጢረ ሥጋዌ ተገልጦ፣ በምሥጢረ ቁርባን ተገልጦ ተሰጥቷል። ኒቆዲሞስና ገማልያል ያዩት እውነት የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ በመካከላችን ነው። የሚቀበለው “አሜን ነአምን ወንትአመን” እያለ ይምጣ። “ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” (ዮሐ 3፡17)
ልጁን ሕይወት አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣ ሕይወታችን በኾነው በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ክብር ምሥጋና ይኹንለት። አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ