መብዛት፣ መጾም እና መቀደስ

 “ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን።” ኤፌ 4፡ 11 “περισσεύητε”

፩ ተሰ ም. ፬፥ ቍ. ፩-፲፫ ፤ ፩ ጴጥ፡ ም. ፩፥ ቍ. ፲፫-ፍ፡ም ፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፲፥ ቍ. ፲፯-፴ ፤ መዝሙር፡ ፺፭(፺፮)፥ ቍ. ፭-፮። ማቴዎስ፡ ም. ፮፥ ቍ. ፲፯-፳፭


የዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት ላይ ነን። ሳምንቱ ቅድስት ይባላል። ከዚኽ ሳምንት ጀምሮ እስከ ሆሳዕና ድረስ ያለው ጊዜ "ጾመ አርብዐ"፣ "ጾመ ኢየሱስ" ይባላል። ለዚኽ እሑድ የተመደቡት ምንባቦች ኹሉም ቅድስና ምን እንደኾነ፣ ለሰው ልጅ ምን ያኽል አስፈላጊ እንደኾነና የቅዱስ ሰው ኑሮም ምን መልክ እንዳለው ይናገራሉ። መዝሙረኛው “ምሥጋናና ውበት ሰማያትን በሠራው በእግዚአብሔር ፊት፣ ቅድስናና ግርማም በመቅደሱ ውስጥ እንደኾኑ” ይዘምራል። ጌታ ኢየሱስም “ስትጾሙ እንደግብዞች አትኹኑ!” እያለ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጾም ምን እንደሚመስል ያስተምራል። ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ፈቃድ የእናንተ መቀደስ ነው” ይላል። ቅዱስ ጴጥሮስ “በኑሯችኹ ኹሉ ቅዱሳን ኹኑ” ይላል። የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊው ቅዱስ ሉቃስም በምጽዋቱና በጸሎቱ የሚታወቀው መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ቅድስናው ይጨምር ዘንድ ጴጥሮስን 40 ማይል ገደማ ርቃ ከምትገኘው ከኢዮጴ ልኮ ሲያስመጣ ሰምተናል። ጾመ ድጓውም “ሰንበትየ ቅድስትየ” እያለ ሰንበትን ከማሞካሸት በተጨማሪ “ተፋቀሩ፡ በምልዓ፡ ልብክሙ። አክብሩ፡ ሰንበተ፡ በጽድቅ፡ ዝግቡ፡ ለክሙ፡ መዝገበ፡ ዘበሰማያት፡ ኀበ፡ ኢይበሊ፡ ወኢይማስን” (በፍጹም ልባችኹ ተፋቀሩ። ሰንበትን በጽድቅ አክብሩ። በሰማያትም ብል የማይበላውና የማይጠፋ ሀብትንን ሀብትን አከማቹ) እያለ እነዚኽኑ ምንባቦች ይዘምራል። እነዚኽን ኹሉ ምንባቦች መብዛት፣ መጾም እና መቀደስ በሚሉ ሦስት ነጥቦች ላይ እንሠራቸው። 


  1. መብዛት

ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ኹሉ በመጻፍ የመጀመሪያ እንደኾነች በሚነገርላት መልእክቱ (49 እስከ 51 ዓም ገደማ) ቅዱስ ጳውሎስ የተሰሎንቄን ምእመናን “ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን፤ እንመክራችኹማለን” ይላል። ከሀገራቸው ሰዎች መከራ ቢቀበሉም በእምነት ጽንተው የቆሙትን የተሰሎንቄን ምእመናን ስለጽናታቸው ያመሰግናቸዋል። ግን፣ የበለጠ እንዲበዙ፣ የክርስቶስ አካል በመኾን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው የመንፈስ ቅዱስ ኑሮ ይበልጥ እንዲጠራ፣ ይበልጥ እንዲጠልቅ አጥብቆ ይመክራቸዋል። እንዲያውም የሚለምናቸው እርሱ ሳይኾን ጌታ ኢየሱስ ራሱ እንደኾነ በግልጥ ያሳያቸዋል። ምን አድርጉ ነው የሚላቸው? “ከዝሙት ራቁ፤ በጸጥታ ኑሩ፤ የራሳችኹን ጉዳይ ጠንቅቁ (በማያገባችኹ አትግቡ!)፣ በእጃችኹ እንድትሠሩ እንለምናችኋለን!” መብዛት ማለት ይኽ ነው። ርኩሰትን መጾም፣ ወሬን መቀነስ፣ በማያገባው ነገር ላይ አስተያየት አለመስጠት፣ ሠርቆ ሳይኾን ሠርቶ ማደር ነው። በጸጥታ መኖር ነው። በዐጭሩ፣ ለኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መብዛት ማብዛት አይደለም። ይልቁንም መጾም፣ መተው፣ መቀነስ፣ መለገስ ነው።   




  1. መጾም 

መብዛት መጾም ነው። መጾም የሚለው የቃሉ ፍቺ ደግሞ መተው ማለት ነው። በዚኽ በመለገስ ሳይኾን ለእኔ፣ የእኔ እያሉ በማከማቸት ፍልስፍና ላይ በተሠራ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ከማከማቸት ይልቅ መጾምን፣ ከመንጠቅ ይልቅ መለገስን መርጦ መኖር ታላቅና ከባድ ገድል ነው። ይኽን ገድል የኖሩ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ። ሰው የመኾን ትርጉም የገባቸው፣ ሕይወታቸውን በሚገባ የኖሩ! ተብለው ይወደሳሉ። ምክንያቱም የሰው ልጅ ውስጡ አንድ እውነት ያውቃል- “The only real sadness, the only real failure, the only great tragedy in life, is not to become a saint.” (“በሕይወት ውስጥ ብቸኛው ሐዘን፣ ብቸኛው ታላቅ ውድቀት፣ ብቸኛው እጅግ አስከፊ ነገር ቅዱስ ሰው አለመኾን ነው”) Leon Bloy። ስለዚኽም ዓለም ይኽን የኑሮ መንገድ የሚሸሸውን ያኽል ያደንቀዋል። የሚጠላውን ያኽል አንዳች ነገሩ ይማርከዋል። ይኽም፣ ለጸዋሚው፣ የዓለምን ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ የሚውጥበትን የመበላላት ማኅበረሰባዊ ሥርዓት “እምቢኝ!” ብሎ ለሚጾመው ሰው ሌላ ፈተና ይደቅንበታል። ይኽ ፈተናም በሰው ልጅ የመወደድ ረኀብ በኩል የሚመጣ ፈተና ነው። የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጥረት ስለኾነ በሰዎች መወደድ ይፈልጋል። ስለኾነም በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ሊያደርጉኝ ይችላሉ ብሎ የሚያምናቸውን ነገሮች ያደርጋል። ተወዳጅ ሊያደርጉኝ ይችላሉ የሚላቸውን ጠባዮቹን ለሌሎች ማሳየት ይወድዳል። በቅርቡ፣ አንድ ሞዛምቢካዊ ፓስተር እንደ ኢየሱስ 40 ቀን እጾማለኹ ብሎ በጠኔ መሞቱን ሰምተናል። በፓስተር ፍራንሲስኮ ባራጃሕ ና በጌታ ኢየሱስ መካከል የነበረው ልዩነት ጌታ ኢየሱስ ወደ ገዳም የኼደው አርባ ቀን ልጹም በሚል የቀን ቆጠራ ጀብድ ሳይኾን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ነው። የመሢሕነት ተልእኮውን ለመጀመር፣ የመሢሕነት ጥሪውን በእግዚአብሔር ፊት ለማየት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጽሙና ጊዜ ለማሳለፍ ነበረ። እኛን ደቀ መዛሙርቱንም ሲያስተምር ትኩረታችን የዶሮና የሽሮ የክክና የክትፎ፣ የዓሣ እና የሽንብራ ዓሣ ልዩነት ላይ ሳይኾን የሰማዩ አባታችን እንዲኾን “ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ! ስትጾም በሥውር ላለው አባታችኹ እንጂ እንደ ጾመኛ ለሰዎች እንዳትታዩ!” ሲል አስተምሮናል። ለምን? ምክንያቱም፣ ጾም በራሱ ግብ አይደለም። የጾም ግቡና ትርጉሙ መቀደስ ነው።  


  1. መቀደስ 

የመብዛት ትርጉሙ መጾም እንደኾነ መጾም ራሱ ደግሞ ትርጉም የሚኖረው ዓላማው መቀደስ ሲኾን ብቻ ነው። የምንተወውን የምንተወው እግዚአብሔርን ፍለጋ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ትዳር የበለጠ ለማደስ፣ ለማጠንከር ካልኾነ ጾም የረኀብ ዐድማ ያኽል እንኳ ትርጉም አይኖረውም። ቆርኔሌዎስ በጸሎትና በምጽዋት የእግዚአብሔርን ፊት ይፈልግ እንደነበረው እኛም ከወሬ፣ በማያገባን ነገር አስተያየት በመስጠት ራሳችንን ከማባከን ሰብሰብ አድርገን፣ ሐሰተኛና የማይጠቅም ወሬ በየሶሻል ሚዲያው ከማራባትና ከማነፍነፍ ጾመን ለእግዚአብሔር ጊዜ ብንሰጥ በምሥጢረ ጥምቀት ተለይተን፣ በምሥጢረ ሜሮን መቅደሱ የኾንንለትን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ድምፁን እንሰማዋለን። ቆርኔሌዎስን የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ወደኾነችው ቤተክርስቲያን የመራው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እኛንም በወሬ ደመና የተጋረዱ ዓይኖቻችንን በብርሃኑ ይገልጥልናል። ከፊታችን ያለውን፣ ዘወትር በቅዱስ ቁርባን “ኑ የእኔ ኅብስት ብሉ! ኑ የእኔን ወይን ጠጡ! ስንፍናን ትታችኹ ኑሩ!” እያለ የሚጠራን የኢየሱስ ክርስቶስ ውበቱ ይገለጥልናል። “ኪርዬ ኤሌይሶን!” እያልን ምሕረቱን ተቀብለን ስንጠጋው በመቅደሱ ይኖራሉ የተባሉት “ቅድስናውና ግርማው” በልባችን መቅደስ ያድራሉ። እርሱ በልባችን ያድራል፤ እኛም በእርሱ እንኖራለን። እርሱ ውበታችን ይኾናል፤ እኛም የብርሃኑን ውበት ለዓለም እያበራን እንኖራለን። ቅዱሱ በእኛ ውስጥ አለና፤ ቅዱሳን እንኾናለን። የልብ ሰላም የአእምሮ ዕረፍት ይኾንልናል፤ ሕይወት ይበዛልናል። እርሱ ራሱ “እኔ ሕይወት ይኾንላችኹ፣ ይበዛላቸውም ዘንድ መጣኹ!” ብሏልና።   

      

ልጁን ሕይወት አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣

 በመጾም መብዛትን ያሳየን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ 

በጸጋው ቤተክርስቲያንን የቅድስናውና የግርማው ማደሪያ ያደረጋት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ 

ዛሬም ዘወትርም ክብር ምሥጋና ይኹንለት! አሜን።።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”