ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው! ኤፌ 5፡ 32
“ዐቢይ ውእቱ ዝ ነገር!”/ “ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው!”/ “τὸ μυστήριον τοῦτο μέγα ἐστίν” ኤፌ 5፡ 32 የትኛው? ሦስት ነጥቦችን ላንሣ፦ እግዚአብሔር ፍጥረትን የወደደበት ዘለዓለማዊ ምሥጢር ከልግስናው፣ ከደግነቱ፣ ከአፍቃሪነቱ ብዛት ህልውና ያልነበረውን ዓለም ካለመኖር ወደመኖር አመጣው፤ ፍጥረትን ኹሉ ወክሎ ሲጠራ አቤት ብሎ ለተወደደበት ፍቅር ምላሽ መስጠት የሚችል የሰውን ልጅም በፍጥረቱ ላይ ጉልላት አድርጎ አኖረ። ይኽን ያደረገበት ምክንያትም የፍጥረት ራስ የኾነው የሰው ልጅ እግዚአብሔር ፍጥረትን ለወደደበት ዘለዓለማዊ ፍቅር የፍቅር ምላሽ በመስጠት ከእርሱ ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር አንድ አንድ ኾኖ እንዲኖር ነው። በዚኽ አንድ በኾነበት ፍቅርም የእግዚአብሔር ብቻ የኾነው ሕያውነት ኹሉ የሰው ልጅ ሀብት ይኾናል። ክብሩን ይለብሳል። ሕይወቱን ይወርሳል። ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስለኾነ ከዐፈር የተበጀው፣ ህልውና፣ ሕያውነት የሌለው የሰው ልጅ ሕያው፣ ህልው ይባላል። ሕያው ኾኖም ፍጥረትን ኹሉ ሕያው ያደርጋል። ራሱ ሕያው ከኾነ አካሉም ሕያው ነውና። ይኽ ከእግዚአብሔር ለፍጥረት የተለገሰ ፍቅር ፍጹም ስለኾነ ከሰው ልጅ የሚገኘው ምላሽ ምንም ቢኾን አይለወጥም። በዚኽ ዘመነ አስተርእዮ በቤተ ክርስቲያን የምናስበው፣ የምናመልከውም ይኽንን ዓለም ሳይፈጠር በፊት ጀምሮ የተወደድንበትና ዘመኑ በደረሰ ጊዜ በእግዚአብሔር ልጅ ሰው መኾን የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው። ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ ለእኛ የነበረው እኛ የእርሱ ኾነን፣ እርሱም የእኛ ኾኖ የመኖሩን ዕቅድ ፈጸመው። ብንበድለው ይቅር ብሎ፣ ብንርቀው ቀርቦ የፍቅሩን ዕቅድ ፈጸመው። ዳግም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ነፋስ እንዳይገባ፣ መተጣጣት እ...