“የለንም!”

ምንባባት፦ ሮሜ ፬፥ ቊ. ፲፬-ፍ፡ም፤ ራእ ፳፥ ፩-ፍ፡ም ፤ ሐዋ ፲፥ ፴፱-፵፬ ፤ መዝ ፸፯(፸፰)፥ ፳፱-፴ ፤ ዮሐ ፳፩፥ ፩-፲፭ ። 

የዛሬው ወንጌል ቢያንስ ሦስት መሠረታዊ የክርስትና ምሥጢሮችን ይነግረናል። 



  1. ትንሣኤና ፍቅር  

በዛሬው ወንጌል ውስጥ ከምናያቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ሥልጣኑን፣ ወይም ትክክለኛነቱን ለማሳየት ከሃይማኖት ተቋማቸው የሚያገኙትን ጥቅም፣ ክብርና ምቾት ለማስጠበቅ ሲሉ ወደገደሉት ካህናትና መምህራን ወይም ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል በግፍ እንዲሰቀል አሳልፎ ወደ ሰጠው ወደ ጲላጦስ ሥልጣኑን ሊያሳያቸው፣ እውነተኛ መሢሕነቱን እግዚአብሔር ከሞት በማስነሣት እንደገለጠ በመመስከር ሊያሳፍራቸው አልኼደም። “እኔ ትክክል ነበርኹ እናንተ ግን ስሕተተኞች፣ ወንጀለኞች ናችኹ” አላላቸውም። ክብሬ ተነካ የምትል አተካራ በእርሱ ዘንድ የለችም። ምክንያቱም እርሱ የሰው ክብር አይፈልግም (ዮሐ 5፡ 42)። ይልቁንም ወደሚወድዱት፣ ወደሚናፍቁት፣ እርሱን በማጣታቸው ሕይወታቸው ወደ ተመሰቃቀለባቸው፣ የትንሣኤውን ዜና ሲሰሙ ደግሞ ግራ ወደ ተጋቡት ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። የዛሬው ወንጌል የሚነግረን ጌታ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጠላቸው ነው። እስከሞት ድረስ የወደዳቸውን ወዳጆቹን ከትንሣኤው በኋላም “በቃ፣ ሥራዬን ጨረስኹ!” የራሳችኹ ጉዳይ ብሎ ጥሏቸው አልኼደም። በፍርኀት ቤት ዘግተው ሲቀመጡ የተዘጋ ቤት ውስጥ ገብቶ፣ ጥርጥር በልባቸው ሲሰፍን እጆቼንና እግሮቼን ዳስሱኝ ብሎ፣ ትንሣኤውን በማመን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን የዘለዓለም ተስፋ ላይ ልባቸውን እንዲያሳርፉ ደጋግሞ ታይቷቸዋል። ዛሬ እንደተነበበልን ደግሞ ኹልጊዜም ከእነርሱ ጋር እንደኾነ፣ ድካማቸውን እንደሚያውቅ፣ ችግራቸውን እንደሚረዳ አሳይቷቸዋል። 


  1. ባዶነትን ማመንና የፊተኛው ትንሣኤ  

ከላይ እንዳየነው ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ፣ ከቤተ ክርስቲያኑ በፍጹም አይለይም። ነገር ግን፣ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ከእርሱ ጋር ናት ማለት አይቻልም። ሰማያዊት የመኾኗን ያኽል የምድራውያኑ እኛ በውስጧ ስላለን ዘወትር በትንሣኤው የተሰጠንን እውነትና ሕይወት እየረሳን ዓሣ ለማጥመድ ስንሯሯጥ እንገኛለን። በቤተሰባዊ ኑሯችንም ይኹን በቤተክርስቲያንነት አገልግሎታችን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ትተን፣ በትንሣኤው የተሰጠንን ሕይወት ራሳችን ዐቃጆች፣ ፈጻሚዎች፣ ገምጋሚዎች ኾነን የምንገኝበት ጊዜ ቀላል አይደለም። ጌታ ሆይ! ምን አደርግ ዘንድ ትወድዳለኽ? ከማለት ይልቅ በራሳችን ሐሳብ ብቻ እናቅዳለን፤ ያቀድነውንም ለማስፈጸም ሌሎችን ማድመጥ፣ ከሌሎች ጋር ለመመካከር እንኳ ፈቃደኞች አንኾንም። ከመነጋገር ይልቅ መከራከር፣ መጣላት ይቀድመናል። ቤተ ክርስቲያንን እያመሳት የሚኖረው ኃጢኣታችን ከሚገለጥባቸው ነገሮች አኳያ አንዱ ይኽ እግዚአብሔርን አለመስማት ነው። እንደእግዚአብሔር ሐሳብ ስለማንጀምር፣ የእግዚአብሔር የኾነው መከናወን ይርቀናል። የምንሠራቸውን ሥራዎች የምንሠራቸው ለእግዚአብሔር እና ለሰው ፍቅር ሳይኾን ለራሳችን ክብር፣ ዝና እና ጥቅም ወይም ሌሎች ላይ በተሰማን እልኽ ምክንያት ስለኾነ ከሥራው ወሬው እየቀደመ ዐየሩን ሲሞላው ይታያል። በየቦታው ስማችንን ለማስጠራት ስንሯሯጥ እንታያለን። እንደብዛታችን፣ እንደሚወጣው ወጪ፣ እንደሚናኘውም ወሬ ጠብ የሚል ፍሬ አይኖርም። አኗኗራችን በፊተኛው ትንሣኤ የክርስቶስን የትንሣኤ ኃይል ለብሰን የምንኖር ሰዎች አለመኾናችንን ይመሰክርብናል። ሌሊቱን ሙሉ እንደክማለን ግን መረባችን ውስጥ አንዳች ነገር አይኖርም። 

በቤታችን ለሚታየው ባዶ መረብ ምክንያቱ በቅዱሳት ምሥጢራት አብሮን የሚኖረውን ጌታ ኢየሱስን መሸሽ ነው። ምሥጢረ ንስሐ የማያውቃቸው ሰዎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ገብተው ይገኛሉ። ቅዱስ ቁርባን የሚሸሹ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ጳጳሳት ጭምር አሉ። ያለ ቅዱሳት ምሥጢራት ክርስቲያን ኾኖ መኖር የሚችል የሚመስለው ሰው ቁጥሩ ብዙ ነው። ብዙ ሰዎቻችን ከቤተ ክርስቲያንነትና ከወንጌላዊነት ይልቅ የአሮጌው አዳም መገለጫ የኾነው ጎሣ ቆጠራና ከመበላላት ፈቀቅ የማይለው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ልጆቻችንን በሞት ፖለቲካ ለሞት ገብረናል። ወጣቶቻችን ከክርስትናችን የሚማርክ ፍሬ አጥተው፣ ከጉባኤያችን እነርሱን የሚያሳትፍ አገልግሎት ተነፍጓቸው ትተውን ኼደዋል። እነዚኽ ኹሉ ለጌታችን የምናቀርባቸው ስጦታችን ነበሩ። ነገር ግን፣ አብሮን የሚኖረውን የጌታችንን ፍቅር ገሸሽ አድርገነዋልና፤ ሌሎችን ልናፈቅር አልቻልንም። ሌሎችም ከእኛ ፍቅር ስላላገኙ አብረውን ሊኾኑ አልወደዱም። ከክርስቲያንነታችን ይልቅ ዓሣ አጥማጅነታችን ውጦን እነሆ መረባችን ባዶ ነው! የሙሽራው ፍቅርና የፍቅር ሥጦታዎች የሚርቡት ጌታ ኢየሱስ የእኛን የወገኖቹን ፍቅር ተርቦና ተጠምቶ “አንዳች የሚበላ አላችሁን?” እያለ ይጠይቃል። በቅርሳ ቅርስ መሸፋፈናችንንና አስፀያፊ ራሳችንን የማወደስ ዲስኩራችንን ትተን ባዶነታችንን ግልጥ አድርገን እውነቱን በመናገር “ጌታ ሆይ! ምንም የለንም!” ማለት አለብን።    


  1. የጌታ ኢየሱስ ግብዣ  

ለድብቅነትና በሰው ፊት ከብሮ ለመታየት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባህላችን ራሳችንን ከፍተን ማሳየት ስላላስተማረን ራሳችንን በግልጥ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበን ጌታ ሆይ! ምንም የለንም ለማለት አዳግቶናል። በዚኽም የተነሣ መረባችንን በየትኛው አቅጣጫ እንደምንጥለው ግራ ገብቶናል። እኛና ባዶ መረባችን በባዶነታችን ባዶ ባደረግናት ባዶዪቱ ጀልባ ላይ ተፋጠናል። ጌታ ኢየሱስ በትንሣኤው ከሰጠን ተበልቶ የማይጠገብ፣ እጅግ የተትረፈረፈ፣ ቤተ ክርስቲያን ኾኖ የመኖር የጸጋ ማዕድ ራሳችንን አርቀናል። ድካማችንን፣ ባዶነታችንን የሚያውቅ ጌታ ኢየሱስ ግን ዛሬም ይጋብዛል፦ “ኑ ምሳ ብሉ!” ፈቃደኛ የኾነ ባዶነቱን አምኖ “ጌታ ሆይ! የለሁም!” እያለ ይምጣ፤ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ እስኪፈልቅ ድረስ ይጠግባል። ክርስቶስ ሞቱም ኾነ ሕይወቱ ለቤተ ክርስቲያን ነውና። 

  

በልጁ ትንሣኤ ሕያው ያደረገን እግዚአብሔር አብ፣ በአንድ ልጁ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በቤተ ክርስቲያን ክብር ምሥጋና ይኹንለት። አሜን።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”