“መንገዱ”
የዛሬ ምንባቦች፦ ሮሜ 1፡1-12፣ 1ኛ ጴጥ. 1፡ 13-22፣ ሐዋ 19፡ 1-11 መዝ 47፡7 ፣ ሉቃ 2፡ 36-42 መዝሙር፦ ተወልደ ኢየሱስ የአስተንትኗችን መነሻ ሐዋ 19፡9 ላይ የሚገኘው “መንገዱ” የሚል ቃል ነው። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ በነበረበት ጊዜ ሲያስተምር አንዳንድ ሰዎች “እልኸኞች ኾነው በሕዝብ ፊት መንገዱን” እንደሰደቡ ይነግረናል። የጥንት ክርስቲያኖች “ራሳቸውን የመንገዱ ተከታዮች” ብለው ይጠሩ ነበረ። የኑሮ ዘይቤያቸውንም “መንገዱ” በግሪክ ὁδὸσ ፣ በሱርስት ደግሞ ܐܘܪܚܐ ፣ በዕብራይስጥ הדרך እያሉ ይጠሩት ነበረ። ስለዚኽ መንገድ ሦስት ነጥቦችን እናንሳና ምንባቦቻችን ምን እያሉን እንደኾነ እንመልከት፦ በእምነት የመታዘዝ መንገድ ይኽ መንገድ ምን ዓይነት መንገድ ነው ብለን ስንጠይቅ መልሱን ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ “ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ” ሲል ይመልስልናል። የራሱን ማንነት ለሮሜ ክርስቲያኖች ሲያስተዋውቅም “በአሕዛብ ኹሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን” ይላል። በሌላ አባባል፣ አሕዛብን ኹሉ አምነው እንዲታዘዙ ማድረግ የቤተክርስቲያን ቋሚ ሥራዋ እንጂ ሌሎች አካላት እስኪ የአካታችነት (inclusivity) ፖሊሲ ስለቀረጹ፣ ወይም እነእገሌ እነ እገሌንም ያካተተ የስብከት መርሐ ግብር አዘጋጂ ስላሏት አይደለም። ክርስቲያኖች የሚኖሩለትም፣ የሚኖሞቱለትም ሌላ ዓላማ የላቸውምና። በእምነት መታዘዝ መጀመሪያ እምነት ይጠይቃል። የሰው ልጅ በተፈጥሮው አማኝ ፍጥረት ነው። ዕውቀቱ ፍጹም ስላልኾነ ሳያምን መንቀሳቀስ አይችልም። ሌላው ቀርቶ በእግዚአብሔር አናምንም የሚሉ ሰዎች እንኳ አለማመናቸውን ባያምኑ ኖሮ የሚያደርጓቸውን ...