“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”

ገላትያ 5፡1፤ ያዕቆብ 5፡ 14 ፤ ሐዋ 3፡ 1፤ መዝ 40፡ 3 ፤ ዮሐ. 5፡ 1 

የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት ላይ ነን። መጻጕዕ ይባላል። ይኽ ሳምንት ጌታ ኢየሱስ ድውያንን መፈወሱን የምታስብበት ነው። በጾመ ድጓዋ “ብውሕ ሊተ እኅድግ ኃጢኣተ በዲበ ምድር፤ እስብክ ግዕዛነ፣ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን፤ አቡየ ፈነወኒ።” (በምድር ላይ ኃጢኣትን ይቅር እል ዘንድ፣ ነጻነትን እሰብክ ዘንድ፣ የዕውራኑን ዓይኖች እከፍት ዘንድ አባቴ ላከኝ) እያለች ወልድ ከአብ ዘንድ ተልኮ ነጻ ያወጣን ዘንድ እንደመጣ ትዘምራለች። በወንጌል የተጠቀሱትን የጌታ የፈወሳቸውን እየጠቃቀሰች ታዜማለች። ከደስታዋም ብዛት “በሰንበት ፈወሰ ዱያነ፤ ወከሠተ አዕይንተ ዕውራን በሰንብተ፤ ፈድፋደ ኪያነ አፍቀረነ።” (በሰንበት ሕሙማንን ፈወሰ፤ የዕውራኑን ዓይኖች ከፈተ፤ እኛን እጅግ ወደደን!) ትላለች። በዚኽ እሑድ የሚነበቡት ምንባባትም ኹሉ ስለ ሕመም፣ ስለ ፈውስ እና ስለ ነጻነት ይናገራሉ። ዋናው ጉዳይ ግን መታመም ወይም መፈወስ ሳይኾን እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሠራውና ዛሬም አካሉ በኾነችውና መንፈሱን በለበሰችው ቤተክርስቲያኑ በሚሠራው ሥራ ለሰው ልጅ የሰጠው ዘለዓለማዊ ግዕዛን (ነጻነት) ነው። በዚኽ አጀንዳ ላይ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሐሳብ ምን ያኽል እንደማይረዱት በዮሐንስ ወንጌል 5 ላይ ያለው ለ38 ዓመታት ታምሞ የኖረው ሰው ታሪክ በግልጽ ያሳያል። በዚኽ ታሪክ ውስጥ ሦስት የተለያዩ አካላትን እንመለከታለን። 

 



አንድ፦ ታማሚው ሰው 

ታማሚው ሰው 38 ዓመት በሥቃይ ኖሯል። ተንገላትቷል። ፈውስ ጠብቆ አላገኘም። ሮጦ መያዝ፣ ሠርቶ መክበር፣ ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትን ማድረግ አልኾነለትም። ስለዚኽ፣ “ከሰዎች አንሻለኹ! ስላነስኹም እኔን የሚወድደኝ የለም። ሰው የለኝም!” ብሎ ያስባል። በሰዎች ላይ መንፈሱ መርሯል። በዚኽ ሰው ሐሳብ መሠረት ተፈውሶ ጤነኛ ያልኾነው፣ ያሰበው ያልተሳካው፣ ያለመው ያልሞላው በሌሎች ሰዎች ምክንያት ነው። የእነ እገሌ እና እገሊት ጥፋት ነው። ጌታ ኢየሱስ ይኽን ሰው ሲያገኘው የሚጠይቀው ጥያቄ ግን ሌላ ማንንም ሳይኾን ራሱን ሰውየውን የሚመለከት ነበረ፦ “ልትድን ትወድዳለኽን?” የሚል። ለምን? የችግሩ ምንጭ ውጪ ሳይኾን ከውስጥ ነበረና። በድጋሚ ሲያገኘውም “ከዚኽ የሚብስ እንዳያገኝኽ ዳግመኛ ኃጢኣትን አትሥራ!” አለው። ስላለፈው ኃጢኣቱ እንደ በርጤሜዎስ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ማረኝ!” ሲል፣ ወይም ዕውር ኾኖ እንደተወለደው ሰው ስለተደረገለት ነገር በምስጋና ለጌታ ኢየሱስ ሲሰግድ አናየውም (ዮሐ. 9)። ይልቁንም በፈሪሳውያን ለተከሠሠበት አልጋን የመሸከም ወንጀል ጌታ ኢየሱስን ተወቃሽ አድርጎ ራሱን ነጻ ለማድረግ ገሠገሠ። በሕይወታቸው ውስጥ ለሚያጋጥማቸው ችግር ኹሉ ሌሎችን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሰዎች መንፈሳቸው መራራ፣ አብረዋቸው ለመኖርም አስቸጋሪዎች ናቸው። እንዲኽ ዓይነት ሰዎች በሥነ ልቡና አጥኚዎች Victimhood mentality ያለባቸው ወይም “የተጠቂነት መንፈስ የተጠናወታቸው” በመባል ይታወቃሉ። ማመስገንም ይቅርታ መጠየቅም አይችሉም። ስለዚኽም፣ የአእምሮ ሰላም የላቸውም። አንድ አሜሪካዊ ጸሐፊ We are not at peace with others because we are not at peace with ourselves, and we are not at peace with ourselves because we are not at peace with God.” (ከሌሎች ጋር ሰላም የሌለን፣ ከራሳችን ጋር ሰላም ስለሌለን ነው። ከራሳችን ጋር ሰላም የሌለን ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ስላልኾንን ነው) ይላል። 


ኹለተኛ፦ አይሁድ 

በዛሬ ምንባቦቻችን ውስጥ ኹለት አይሁድ እናገኛለን። አንደኛው ጌታ ኢየሱስን “ሰንበትን የሚሽር” እያለ የሚከስሰው ነው። ኹለተኛው ደግሞ ከጣዖት አምልኮ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን የገላትያን ምእመናን በ“ባዕድ ወንጌል” (ገላ 1፡ 6) ስብከት የሚያውከው ነው። ይኽ ባዕድ ወንጌል “የሙሴን ሕግ ካልጠበቃችኹ፣ ምግብ ርኵስና ንጹሕ እያላችኹ ካልለያችኹ፣ ወንዶች ካልተገረዛችኹ፣ ባጠቃላይ እንደ አይሁድ ካልኖራችኹ የቤተ ክርስቲያን አባላት መኾን፣ የመሢሑን ተስፋ መውረስ አትችሉም” እያለ ባዕድ ወንጌል የሚሰብከው ነው። ኹለቱም የሚሠሩበት መንፈስ አንድ ዓይነት ነው። ይኽ መንፈስ ሕግና ገበያ እንጂ “በፍቅር የሚሠራ እምነት” አያውቅም። እግዚአብሔር በልጁ የሰጠውን ፍጹም ጸጋ ትቶ የራሱን ጽድቅ እንደሐውልት በማቆም በእግዚአብሔር ፊት ነጥብ ማስቆጠር ይሻል። ያስቆጠረውንም ነጥብ ሰብስቦ እግዚአብሔርን “እግዚአብሔር ሆይ! የሙሴን ሕግ ስለምጠብቅ፣ ስለተገረዝኹ፣ የተመረጠ ምግብ ስለምበላ፣ ጾም ስለምጾም፣ ምጽዋት ስለምመጸውት፣ አሥራት በኩራት ስለማወጣ፣ ወዘተ. እንዲኽ አድርግልኝ!” ብሎ እግዚአብሔርን ሊያስገድድ የሚዳዳው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የገበያ ድርድር ማድረግ የሚቃጣው መንፈስ ነው። ይኽ አስተሳሰብ የተጠናወተው ሰው “ዐውቃለኹ! ነቅቻለኹ! በቅቻለኹ!” ብሎ ስለሚያምን ማንም እርሱን ሊያስተምረው የሚችል አይመስለውም። ይልቁንም ሌሎች ሰዎች ኹሉ የእርሱን መንገድ መከተል አለባቸው ብሎ ያስባል። አእምሮውም አንደበቱም ሰዎችን በማረም፣ በመተቸት ተጠምደው ውለው ያድራሉ። በዓለም ውስጥ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ከመኖር ይልቅ አካባቢውን በአምሳሉ ሊፈጥራት ይታገላል። ይኽ የአይሁድ መንፈስ ለትችት ፈጣን ነው። በሰንበት ለ38 ዓመታት የታመመ ሰው መፈወሱን ከማድነቅ ይልቅ አልጋ መሸከሙን ሊተቹት የፈጠኑት ለዚኽ ነው። ጌታ ኢየሱስ ግን ለትችታቸው የነበረው መልስ “አባቴ እስከዛሬ ይሠራል።። እኔም ደግሞ እሠራለኹ።”  የሚል ነበረ። 


ሦስተኛ፦ ጌታ ኢየሱስ 


ጌታ ኢየሱስ ከላይ ካየናቸው ኹለት ወገኖች የተለየ ነው። አጀንዳው አባቱ እንዲሠራ የሰጠውን ሥራ በፍጹም ታዛዥነት መሥራት ነው። ለሚሠራው ሥራ ምክንያቱ ለአባቱ ያለው ፍጹም ፍቅር ብቻ ነው። ከሰዎች ዕውቅና ወይም ውዳሴ ወይም ልዩ ጥቅማ ጥቅም አይፈልግም። አባቱ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው እርሱም ደግሞ ለሚወድዳቸው ሕይወትን መስጠት ይሻል። የዚኽ ምክንያቱም ለአባቱ ያለው ፍጹም ፍቅርና ታዛዥነት፣ እንዲኹም ለሚወድዳቸው የሰው ልጆች ያለው ለጋስ ፍቅር ነው። የሥራው ምክን ያት ፍቅር ስለኾነም የሰው ትችትም ኾነ ምሥጋና ጉዳዮቹ አይደሉም። የሚያደርገውን በፍጹም ነጻነት ያደርጋል። የሚሠራውን በፍጹም ነጻነት ይሠራል። የማንም አስተያየት ባርያ አይደለም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቲቶ መልእክት ትርጓሜው ላይ “የመከበር ምኞት ምርኮኞቿን የምታዝዘውን ያኽል የትኛውም ጌታ ባሮቹን አያዝዝም። መታዘዛቸው በጨመረ ቁጥርም ትእዛዞቿ እየጨመሩ ይኼዳሉ።” ይላል። ጌታ ኢየሱስ ከዚኽ ነጻ ነው። “እኔ ከሰው ክብርን አልቀበልም” (ዮሐ 5፡ 41) እንዳለ። አካሉ ለኾነችው ለቤተ  ክርስቲያንም ይኽን ነጻነት ሰጥቷታል። ክርስቲያን እነእገሌ ይዩኝ ብሎ፣ እነእገሊት ይስሙኝ ብሎ የሚያደርገው ነገር የለውም። ምክንያቱም፣ ለዓለም እና ለክብሯ ሞቶ ለእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ለመኖር በምሥጢረ ጥምቀት ከክርስቶስ ተዋሕዷልና። የክርስቲያን ዓላማው በምሥጢረ ቁርባን ተዋሕዶት ከሚኖረው ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንጂ ከሰው የሚገኝ ክብር፣ ዝና፣ ዕውቅና፣ ውዳሴ፣ ወዘተ. አይደለም። ከሰው የሚሰጥ የውሸት ክብርና እንደጤዛ ብን ብሎ የሚጠፋ ጥቅም ባሮች ኾነን እንድንኖር ሳይኾን “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናልና።”


ከኃጢኣተኝነት ነጻ አውጪያችን አድርጎ ልጁን የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣ የነጻነት ዘውዳችን በኾነው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በነጻነት ቅዱስ መንፈሱ በመላት በቤተክርስቲያን ክብር ምሥጋና ይኹንለት።    


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)