የደነደነ ልብ፣ የታወረ ዐይን፣ የተሰቀለ መሢሕ

የዛሬ የግጻዌ ምንባቦች፦ ፩፡ ቆሮ፡ ም. ፪፥ ቍ. ፩-ፍ፡ም ፤ ፩፡ ዮሐንስ፡ ም. ፭፥ ቍ. ፩-፮ ፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፭፥ ቍ. ፴፬-ፍ፡ም ፤ መዝሙር ፬፥ ቍ. ፪-፫ ፤ ዮሐንስ፡ ም. ፱፥፩-ፍ፡ም ። የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ጌታ ኢየሱስ “እኔ የማያዩት እንዲያዩ፣ የሚያዩት እንዲታወሩ እኔ ወደዚኽ ዓለም ለፍርድ መጣኹ” ሲል ያስሰማናል። መዝሙረ ዳዊት “ልባችኹን እስከመቼ ታደነድናላችኹ?” እያለ ይጠይቃል። በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ሉቃስ ጴጥሮስና ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደኾነ በማስተማራቸው እንደተገረፉ ይነግረናል። ቅዱስ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ምእመናን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከተገደለው ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ አንዳችም ነገር እንዳልሰበከላቸው ሲያስታውሳቸው ሰምተነዋል። የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ መልእክትም “ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?” ብሎ ይጠይቀናል፤ ያጠይቀንማል። ያሬዳዊው መዝሙርም ጊዜው ዘመነ አስተምህሮ መዝሙሩም እሑዱ “መጻጕዕ” እንደሚባል መዝሙሩም በዮሐንስ ወንጌል የተነበበውን ምንባብ “ይቤሉ እስራኤል ኢሰማዕነ ወኢርኢነ እም አመተፈጥረ ዓለም ዘዕውሩ ተወልደ” (ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕውር ኾኖ የተፈጠረውን ሰው ዓይኖች ያበራ ሰው አላየንም አልሰማንም አሉ” እያለ ያዜማል። በዐቢይነት የምናያቸው ሦስት ነጥቦች ማንሣት እወድዳለኹ፤ የደነደነ ልብ፣ የታወረ ዐይን፣ የተሰቀለ መሢሕ። የደነደነ ልብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ተሰጥቷቸው ከምናገኛቸው ቃላት ውስጥ ልብ አንዱ ነው። የግሪኮሮማን ሥልጣኔና ቃላት ከመግነኑ በፊት በነበረው የሴማውያን ባህል ልብ የሚለው ቃል ማወቅን፣ መረዳትን፣ ማስተዋልን ያመ...