በእርሱ ኾናችኹ ተሞልታችኋል

 “በእርሱ ኾናችኹ ተሞልታችኋል” (ቆላ. ፪፥ ቍ. ፲-፲፮ ፤  ፩ዮሐ፡ ም. ፪፥ ቍ. ፳፭-ፍ ፤ ሐዋ፡  ፳፪፥ ቍ. ፯-፳፪ ፤ ማቴ ፪፥  ቍ. ፳፪-ፍ፡ም)

ባለፈው ሳምንት ልደትን፣ ትናንት ደግሞ ግዝረትን አከበርን። ምንባቦቹ ይኽንን ይዘው የነቢያት ትንቢት መፈጸሙን፣ ጌታ በሥጋ መገለጡን፣ ለቤተ ክርስቲያንም ጸጋውን ማደሉን ይነግሩናል። እኛንም ይኽን እንዲያው የተሰጠንን ጸጋ ታላቅነት እንድናስተውለው፣ እንድንኖረው ያሳስባሉ። ሦስት ነጥቦችን እናንሳ፦

  1.   የእመቤታችን ዝምታ (የቤተክርስቲያን ሌላኛው ሥርዓተ አምልኮ)


የቤተ ክርስቲያን አምልኮ ሲባል ብዙዎቻችን የምናስበው እንደከበሮና ጸናጽል ያሉ የሙዚቃ መሣሪያዎቻችንን ወይም የሰዓታትና የማሕሌትን ያሬዳዊ ዜማን ይኾናል። ስሕተትም አይደለም። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን አምልኮ ድምፃዊ ብቻ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ኖሮዋ ኹሉ አምልኮ ስለኾነ ድምፅ በማታወጣበት ጊዜም አምልኮዋ አይቋረጥም። ይኽ አምልኮም በእመቤታችን ዝምታ ውስጥ የሚከናወን ነው። እንዴት? ወዳነበብነው የማቴዎስ ወንጌል እንኺድ። ጌታ ኢየሱስ “በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ” በማለት ከልደት እስከ ጥምቀት የነበረውን
በእመቤታችን የድንግል ማርያም ዝምታ ውስጥ ብቻ እንድናስተውለው የተሰጠንን የጌታችንን የልጅነት፣ የጉርምስና እና የወጣትነት እድሜ ይጠቁመናል። የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ኾነ፤ በየጥቂቱ አደገ። ከእናቱ ዕቅፍ እስከ ጉልምስና ለቤተሰቦቹ እየታዘዘ አደገ። የቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ የጌታችንን ሕይወት እየተከተልን ወደ ጥምቀት እንድንኼድ እየጋበዘን ነው፣ በጽሙና፣ በአርምሞ፣ የተሰጠንን እንድናስተውል እየተጋበዝን ነው። ለምን?  

  1. የተሰጠን ጸጋ ከቃላት በላይ ነው። 

በእውነት የተሰጠን ጸጋ ታላቅ ነው።  ቅዱስ ጳውሎስ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ኹሉ በሰውነት (σωματικῶς) ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣን ኹሉ ራስ በኾነ በእርሱ ኾናችኹ ተሞልታችኋል (πεπληρωμένοι)” ይለናል።  አምላክ ሰው ኾኗልና፣ እግዚአብሔር የሥጋ ዘመዶቹ አድርጎናልና ኹሉን የሚሞላው እርሱ ራሳችን ኾኖልን ሙሉ ሰዎች ኾነናል። አዲሱ አዳም ሕያው ክርስቶስ ራሳችን ስለኾነልን በድን አካል አይደለንም፤ ሕያዋን ነን እንጂ! ልባችንንም እርሱ ስለሞላው በኃጢኣተኝነት ተይዘን በማይረካ የሥጋ ፍላጎትና የዓይን አምሮት ሰቀቀን ውስጥ አንኖርም። ከኹሉም በላይ የዘለዓለም ጥያቄያችን ተመልሶልናል። እግዚአብሔርን ዳግም ላናጣው አግኝተነዋል። ከእርሱም ጋር በአንድነት ልንኖር በምሥጢረ ሥጋዌ በተዋሕዶ ቃል ኪዳን ተሳሥረናል። እርሱ ራሳችን እኛም አካሉ ኾነናል። አካሉ የኾነችው ቤተ ክርስቲያን ስለኾንንም ሙላቱ ተብለናል። በዚኽ ምድር ላይ የምንኖርበት ምክንያትም ይኽንን ሙላት በምድር ነዋሪዎች ልብ ውስጥ ኹሉ ለመሙላት ነው። ሌላ ዓላማ የለንም። ካለንም በንስሐ መራገፍ ያለበት የሞትም መንገድ ነው። 

  1. ሙላታችንን ሲገለጥ 

በምሥጢረ ጥምቀት የተካፈልነው፣ በምሥጢረ ሜሮን የተቀበልነው፣ በቅዱስ ቁርባን ዕለት ዕለት የምንቀበለው ሙላት ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ፦ “እናንተስ፡ ከእርሱ የተቀበላችኹት ቅባት በእናንተ ይኖራል፤ ማንም ሊያስተምራችኹ አያስፈልጋችኹም።” ይለናል። ይኽም በነቢዩ ኤርምያስ እንዲኽ ተብሎ የተነገረው ፍጻሜ ነው፦ “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፤… ሕጌን በልቡናቸው አኖራለኹ፤ በልባቸውም እጽፈዋለኹ፤ እኔም አምላክ እኾናቸዋለኹ፤ እነርሱም ሕዝብ ይኾኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን፡ 'እግዚአብሔርን ዕወቅ'  ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፤ ይላል እግዚአብሔር።” (ኤር 31፡33)።  በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የምንካፈልው የእግዚአብሔር ሙላቱ በእኛ ሲኖር ክፉና ደግ፣ የእግዚአብሔር መንፈስና የሰይጣን መንገድ አይደበላለቁብንም። እንኳን እኛ እኛን የሚያገኙ ኹሉ የእግዚአብሔር መገኘት ይሰማቸዋል። ቃሉ ያጽናናቸዋል። ሰላሙ ያሳርፋቸዋል። ድንግል ስትወልደው ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው እንደመጡ፣ በእኛ ልብ ውስጥ ተወልዶ ሲያገኙትም መዝሙረኛው እንዳለው ወርቅ ከዓረብ ያመጡለታል፤ ወደእርሱም ዘወትር ይጸልያሉ፤ ዘወትርም “የክርስቲያኖች አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ ይባረክ!” እያሉ ያመሠግናሉ።  

በልጁ ሰው መኾን ልጆቹ ያደረገን፣ ቤተ ክርስቲያንንም በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሞላት 

ልዑል እግዚአብሔር አብ 

ክብር ምሥጋና ይኹንለት።        


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”