የዓለሙን ኃጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ
“እነሆ! የዓለሙን ኃጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” ዮሐ. 1፡17
ክርስቲያናዊ ሰማዕትነትና ፖለቲካ
ባለፈው ሳምንት ካነበብነው ሮሜ 13 ጋር ይቃረናልን?
ጳውሎስ ሰበከን፤ ዮሐንስ መጥምቁ አሳየን።
ክርስቲያኖች በጎ ከሚሠሩና በጎ ኅሊና ካላቸው ጋር ኹሉ በመተባበር ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ነገር ግን፣ ይኽ ተሳትፏቸው በኹለት መርሖች ላይ ይመሠረታል።
ሀ. የሰው ልጅ ከፈጣሪው ተነጥሎ ሊታሰብ አይችልም። የታሪክ አጋጣሚ የወለደው ወለፈንዴ አይደለም። (ማርክሲዝም፣ ሂዩማኒዝም፣ ኢንላይተንመንት፣ ወዘተ.)
ለ. ህላዌ ስጦታ ስለኾነች ማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ከተፈጥሯዊ የሞራል ሕግ ተቃርኖ መቆም አይችልም። ልቁም ቢል ራሱን ያጠፋል።
የዮሐንስ ምስክርነት እነዚኽ ላይ የተመሠረተ ነበረ። ምስክርነቱም እስከመጨረሻው የሕይወቱ ጠብታ ድረስ ነበረ። ለምን? ምክንያቱም የዓለም ችግር በእግዚአብሔር መገኘትና በኃጢኣት መወገድ እንጂ በፖለቲካዊ ሥርዓት፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ በቴክኖሎጂ ምጥቀት አይፈታም። ዞሮዞሮ መዝጊያው ሞት ነው። ከሜሶጶጣሚያ እስከ ሮም፣ ከሮም እስከ አሜሪካ ታሪኩ አንድ ነው። ፕሌቶም ታሪክም በግልጽ ይኽን አዙሪት ይነግሩናል። ከታሪክ የምንማረው ያፈጠጠ እውነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስም የመጀመሪያው ከተማ ሠሪ ቃየን እንደኾነ ይነግረናል።
ስለዚኽ ዮሐንስ “ሄሮድስ ኤዶማዊም ቢኾን ከሮማውያን ይልቅ ዘሩ ለእኔ ይቀርበኛል” ብሎ በዘረኝነት ዐይኖቹን አላሳወራቸውም። ዛሬ ማተብ አሥረው፣ መስቀል ጨብጠው፣ “የእኛ ዘር ጥራቱ፣ ምጥቀቱና ሥልጣኔው!” እያሉ ሲያስቡና ሲናገሩ የሚውሉ ሰዎች ዮሐንስ ይመሰክርባቸዋል። እርሱ የሰው ልጅን ኑሮ ያከፋው የኃጢኣት ጨለማ እንደኾነ ያውቃል። የሰው ልጅ የችግሩ ኹሉ ሥር እግዚአብሔርን ማጣቱ፣ የጸጋ ድኽነቱ፣ ሕይወት አልባነቱ እንደኾነ ተረድቷል። ስለዚኽም ትክክለኛውን መፍትሔ ሊያመለክት፣ ስለብርሃን አስፈላጊነት ሊመሰክር መጣ። ሲመሰክርም እንዲኽ አለ፦ “እነሆ የእግ. በግ!”
ሄሮድያዳ ምን ፈለገች?
ሄሮድያዳ ከብዙዎቻችን የተለየች ሰው ነበረችን? የኑሮዋ ዓላማ ምን ነበረ? ሄሮድስ ፊልጶስን ትታ ሄሮድስ አንቲጳስን ያገባችው ሄሮድያዳ መሻቷ አንድ ነገር ብቻ ይመስላል፤ ምቾት። የበለጠ ምቾት። የተሻለ ምቾት። የተቀደደ ልብ። ወደ 25 ዓመት ገደማ አብራ የኖረችው የልጅነት ባሏን ትታ በዕድሜ ቀረብ የሚላትን ታናሽ ወንድሙን አገባች። ታናሽ ወንድሙም የኖረች ሚስቱን ፈትቶ ሄሮድያዳን አገባ። ለምን? የወንድሙ ሚስት ስለ ተመቸችው። ሄሮድስ ፊልጶስ ምናልባት የአባቱን የታላቁን ሄሮድስ ፈለግ ተከትሎ 10 ሚስትና ማለቂያ የሌላቸው ቁባቶች ሰብስቦ ይኾናል። ስለዚኽም ለ25 ዓመት ገደማ አብራው የኖረችው ሚስቱ ጥላው ስትሄድ ምንም ያለ አይመስልም።
ምቾት አምላኪ ሰው በአምላኩና በእርሱ መካከል የሚገባውን ማንኛውንም ነገር በተቻለው መንገድ ኹሉ ከማስወገድ ወደ ኋላ አይልም። ለምን? አምልኮ ነዋ! አምልኮ መሥዋዕት መጠየቁ አይቀርም። በሕይወታችን የምንኖርለት ዓላማ ሌሎቹን ነገሮች ኹሉ የምንሠዋለት አምላካችን ነው።
ዮሐንስ ለምን ተቆጣ?
የፊት ለፊት ምክንያቱ ሌዋውያን 20፡21 ላይ የተጻፈውን የወንድምኽን ዕርቃን አትግለጥ የሚል ሕግ ስለተጣሰ። ውስጣዊ ምክንያቱ ግን በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት መሪዎቹ እግዚአብሔርን ትተው ምቾት ሲያመልኩ፣ እግዚአብሔርንና ሕዝቡንም ለምቾታቸው ሲሠዉ ስለተመለከተ ነው። እናንተ የዕለት ዕለት ኑሯችኹን የምትሠዉት ለማን ነው?
ክርስትናና አካል
በሐዋርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ክርስቲያን መኾን ፍጹም አካላዊ የኾነ ጉዳይ ነው። ፕላቶኒክ ሐሳባዊ ፍልስፍና አይደለም። አካላዊ ኾኖ ተጀምሮ አካላዊ ኾኖ የሚጠናቀቅ፣ ፍጹም ከሥጋና ደም ጋር የተዋሐደ ነገር ነው። ክርስቲያን ስንኾን በአካል ተጠምቀን፣ በአካል በሜሮን ከብረን፣ በአካል ቆርበን፣ በአካል ተቀድሰን፣ ምድሪቱንም በአካላዊ ኑሯችን ቀድሰን የምንኖረው ኑሮ ነው። በቅዱስ ጥምቀት የክርስቶስ አካል የኾነውን አካላችንን በክርስቶስ አካልነቱ፣ በቅዱስ ቁርባን ከምናቀርበው የክርስቶስ አካል ጋር አንድ አድርገን፣ አንድ ኾነን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መሥዋዕት ኾነን የምናቀርብበት ኑሮ ነው። ለዚኽም ነው ካህኑ መሥዋዕቱን እንደሚያጥነው እኛን እየዞረ የሚያጥነን። በዮሐንስ የምናየው፣ የምናስበው እስከመጨረሻዪቱ ሕቅታ ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር፣ በእግዚአብሔር ውስጥ፣ ለእግዚአብሔር ክብር የሚኖር ኑሮ፣ በልባችን ዙፋን ላይ ጌታ ኢየሱስን አንግሦ፣ ብርሃኑን ተሸክሞ ለዓለም ኹሉ እያሳዩ “የዓለምን ኃጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!” እያሉ ዓለሙን ወደ ብርሃን፣ ወደ ዕረፍት፣ ወደ እውነት መጥራት በምሥጢረ ጥምቀት የተጠራንለት ከቅዱስ ቁርባን ጋር በነፍስ በሥጋ አንድ ኾነን የምንኖርበት ኑሮ ነው። የዓለሙ ችግር ኃጢኣት፣ መፍትሔውም እኛን ሥጋውያኑን ወድዶ ሥጋ የኾነው የዓለሙን ኃጢኣት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነውና።
ልጁን የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣ ራሱን የሰጠን እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በቤተ ክርስቲያን ጸጋ የክርስቶስ ብልቶች ያደረገን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ይኹንለት።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ