የደነደነ ልብ፣ የታወረ ዐይን፣ የተሰቀለ መሢሕ

የዛሬ የግጻዌ ምንባቦች፦ ፩፡ ቆሮ፡ ም. ፪፥ ቍ. ፩-ፍ፡ም ፤ ፩፡ ዮሐንስ፡ ም. ፭፥ ቍ. ፩-፮ ፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፭፥ ቍ. ፴፬-ፍ፡ም ፤ መዝሙር ፬፥ ቍ. ፪-፫ ፤ ዮሐንስ፡ ም. ፱፥፩-ፍ፡ም ። 

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ጌታ ኢየሱስ “እኔ የማያዩት እንዲያዩ፣ የሚያዩት እንዲታወሩ እኔ ወደዚኽ ዓለም ለፍርድ መጣኹ” ሲል ያስሰማናል። መዝሙረ ዳዊት “ልባችኹን እስከመቼ ታደነድናላችኹ?” እያለ ይጠይቃል። በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ሉቃስ ጴጥሮስና ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደኾነ በማስተማራቸው እንደተገረፉ ይነግረናል። ቅዱስ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ምእመናን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከተገደለው ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ አንዳችም ነገር እንዳልሰበከላቸው ሲያስታውሳቸው ሰምተነዋል። የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ መልእክትም “ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?”  ብሎ ይጠይቀናል፤ ያጠይቀንማል። ያሬዳዊው መዝሙርም ጊዜው ዘመነ አስተምህሮ መዝሙሩም እሑዱ “መጻጕዕ” እንደሚባል መዝሙሩም በዮሐንስ ወንጌል የተነበበውን ምንባብ “ይቤሉ እስራኤል ኢሰማዕነ ወኢርኢነ እም አመተፈጥረ ዓለም ዘዕውሩ ተወልደ” (ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕውር ኾኖ የተፈጠረውን ሰው ዓይኖች ያበራ ሰው አላየንም አልሰማንም አሉ” እያለ ያዜማል። 

በዐቢይነት የምናያቸው ሦስት ነጥቦች ማንሣት እወድዳለኹ፤ የደነደነ ልብ፣ የታወረ ዐይን፣ የተሰቀለ መሢሕ።     

  1. የደነደነ ልብ 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ተሰጥቷቸው ከምናገኛቸው ቃላት ውስጥ ልብ አንዱ ነው። የግሪኮሮማን ሥልጣኔና ቃላት ከመግነኑ በፊት በነበረው የሴማውያን ባህል ልብ የሚለው ቃል ማወቅን፣ መረዳትን፣ ማስተዋልን ያመልክታል። በአማርኛ ዛሬም ድረስ “ልብ አድርጉልኝ!” ይባላል። የከፍታውን ያኽል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ከሚነቀፉ ነገሮች አንዱ “የደነደነ ልብ” ነው። የደነደነ ልብ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት አይችልም። ራሱን ለመጠበቅ፣ ጥቅሙን ለማስከበር፣ ፍላጎቱን ለማስፈጸም ጡንቻውን አፈርጥሟል፤ ጥጥር ድድር ብሏል። እየተከተለ ከክፋት መንገዱ እንዲመለስ የሚጠራው የእግዚአብሔር ኮቴ አይሰማውም። የሚሰማው ድምፅ ካለ በውስጡ የሚመላለሰውን የራሱን የሐሳብ፣ የእርሱ አጀንዳና ዕቅድ፣ ትልምና ግብ ብቻ ነው። ይኽን ብያኔ ይዘን ወደ ምንባባችን ስንመለስ በምስባክ የሰማነው የመዝሙረኛው ቃል የሰው ልጆችን “እስከ ማእዜኑ ታከብዱ ልበክሙ?” እያለ ይጠይቃል። የግእዙ መጽሐፍ ቅዱሳችን የሰባው ሊቃናት ትርጉም ላይ ስለሚመሠረት ግሪኩን ተከትሎ የኼደ ነው። ዕብራይስጡ ግን ልባችኹን እስከመቼ ታከብዳላችኹ በማለት ፈንታ “עַד־מֶ֬ה כְבוֹדִ֣י לִ֭כְלִמָּה  (“አድ ሜህ ክቮዲ ሊክሊማህ”) እስከመቼ ክብሬን ታዋርዳላችኹ? ይላል። ቃሉ ቢለያይም ምሥጢሩ አንድ ነው። ደንዳና ልብ ያለው ሰው እግዚአብሔርን ከማክበር ይልቅ እግዚአብሔር እርሱን እንዲያከብረው፣ እንዲያሽሞነሙነው፣ በሰዎች ዓይን ከፍ ያለ ቦታ እንዲያስገኝለት ይሻል እንጂ እግዚአብሔርን ማክበር አጀንዳው አይደለም። እግዚአብሔርን አከበርኹ ቢልም ከእግዚአብሔር ወይም ከሰዎች አንዳች ክብር ወይም ጥቅም ወይም ዝና ማግኘት ፈልጎ ነው። ደንዳና ልብ ማፍቀር አይችልም። ደንዳና ልብ “ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ እርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣ የበጎች ጉሮኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል። በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለኹ!” ማለት አይችልም (ዕንባቆም 3፡ 17_8)። ፍቅር አያውቅማ! ፍቅር አይገባውም።  



እንግዲኽ የዘማሪው ጥያቄጥያቄ “ይኽን ደንዳና ልባችኹን ከላያችኹ ላይ የምታራግፉት መቼ ነው? እግዚአብሔር የእናንተን “የተቀደሰ” ማብቂያ የሌለው የምቾት ጥማት፣ የዝና ጥማት፣ የክብር ጥማት፣ የሀብት ጥማት፣ ወዘተ. እንዲያሟላላችኹ ለማዘዝ መሞከራችኹን የምትተዉት መቼ ነው? እግዚአብሔርን በመሥዋዕታችኹ ስባትና በስጦታችኹ ብዛት ለመደለልና ለማባበል መሞከራችኹን የምታቆሙት መቼ ነው? የእግዚአብሔርን ሐሳብ ብቻ የምትከተሉት መቼ ነው? እግዚአብሔርን ስለእግዚአብሔርነቱ የምታከብሩት መቼ ነው? እግዚአብሔርን ስለእግዚአብሔርነቱ የምታፈቅሩት መቼ ነው? የእግዚአብሔር አጀንዳ አጀንዳችኹ የሚኾነው መቼ ነው?” ይላል። ይኽ ጥያቄ ለሰውልጅ መንፈስዊ ጤንነት እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ልብ ከደነደነ ዓይን ቢገለጥም የእግዚአብሔርን አሠራር፣ የእግዚአብሔርን መንገድ ማየት አይችልም። አባቶች “ልብ ካላየ ዓይን አያይም” እንዲሉ።  ዓይን ካላየ ደግሞ እግር አይከተልም።

  1. የታወረ ዓይን  

የታወረ ዓይን አባቱ የደነደነ ልብ ነው። በራስ አጀንዳ የታወረ ዓይን ከራስ ወዳድነት ሽፋሽፍቱ አልፎ ከፊቱ እየተከናወነ ያለውን የእግዚአብሔርን አሠራር ማየት ይሳነዋል። ለእግዚአብሔር የ“አድርግልኝ!” አጀንዳ ብቻ ሳይኾን የአሠራር ቅደም ተከተልም ይሰጣል። ከዚያች እርሱ ለክቶ፣ ቆርጦ ከተለማትና “ትክክለኛዋ የእግዚአብሔር አሠራር” ብሎ ስም ከለጠፈላት  መንገድ በሌላ መንገድ የእግዚአብሔርን አሠራር ማየትና መከተል አይችልም። ፈሪሳውያን የኾኑት ይኽንን ነው። ከፊታቸው ዓይኖች ያልነበሩት ሰው ዓይኖች ሲያገኝ እያዩ እነርሱ በባህላቸው፣ በወጋወጋቸውና በአስተምህሯቸው ቀንብበው ካበጁትና ከሚያስቡት መንገድ አልስማማ ቢላቸው “ይኽ ሰው ኃጢኣተኛ እንደኾነ እኛ እናውቃለን!” ብለው ደመደሙ። ጌታ ኢየሱስ ማንም ሌላ ሰው ያላደረገውን ነገር እያደረገ፣ ማንም ሌላ ሰው ከሚያስተምረው ልዩ በኾነ ኹኔታ እያስተማረ ያዩታል፤ ነገር ግን፣ የእነርሱን መስፈሪያ አላሟላ ስላላቸው፣ ሲብስም ከንቱ ትምህርቶቻቸውን እየገለጠ ስላስተማራቸው ሲጠብቁት የነበረው መሢሕ መሆኑን መቀበል አቃታቸው። “ከጓሮ ያለ ጠበል ቆዳ መንከሪያ ይኾናል!” እንዲሉ ከጌታ ትንሣኤ በኋላም ትናንት በዓሣ አጥማጅነት የሚያውቋቸው ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አደባባይ “ኢየሱስ ከሞት ተነሥቷል! መሢሑም እርሱ ነው!” እያሉ ሲናገሩ እያዩዋቸው ሊቀበሏቸው አልቻሉም። ምክንያቱም በእነርሱ ስሌት “መሢሑ ሲመጣ የእስራኤልን ጠላቶች ጭብጥ፣ ርግጥ፣ ድፍጥጥ አድርጎ አጥፍቶ የእስራኤልን ኤምፓየር ይመሠርታል፤ እኛ እስራኤላውያን (የእግዚአብሔር የበኩር ልጆቹ) ደግሞ በዚኽ ኤምፓየር እየተሰገደልን እንኖራለን” የሚል ንድፈ ሐሳብ ነበራቸው። ንድፈ ሐሳቡን በበርካታ የነቢያት መጻሕፍት ጥቅሶች የታጀበ እንደነበረም ጥርጥር የለኝም። (የራስን ንድፈ ሐሳብና ባህላዊ አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐረፍተ ነገርና ሐረግ እየቦጫጨቁ ለማስደገፍ መሞከር፣ መጽሐፍ ቅዱስን መከተል አይደለም።) እና ይኽን ልብ የሚያሞቅ፣ የፖለቲካዊ ድልን የተስፋ ዳቦ የሚያስገምጥ ንድፈ ሐሳብ ትተው አንድ ለራሱ ማረፊያ ቤት እንኳ ያልነበረው፣ በአደባባይ ዕርቃኑን ተሰቅሎ የተገደለ ኢየሱስ የሚባል የናዝሬት ሰው መሢሕ ነው ብለው ይመኑ? ያውም ገሊላ ከሚባል ገጠር የመጡ ገጠሬዎችን ሰምተው?¡ እርሱ ከናዝሬት፣ ምስክሮቹ የገሊላ ዓሣ አጥማጅ ገጠሬዎች እንዴ? የእግዚአብሔር መሢሕ ኢየሩሳሌምን ማን ወስዶበት ነው የናዝሬት አቧራ ላይ የሚወድቀው? ስለዚኽ፣ ሐዋርያቱን ጌታ ኢየሱስ ይጠበቅ የነበረው መሢሕ እንደኾነ ሲያስተምሩ ፈሪሳውያን ተረበሹ። “በዚኽ ሰው ስም አታስተምሩ!” ብለው ደበደቧቸው። ልብ ከታወረ ዓይን አያይም። 

  1. የተሰቀለ መሢሕ

ቅዱስ ጳውሎስ ይኽን የፈሪሳውያን ትምህርት ተቀብሎ የኖረ ፈሪሳዊ ነው። ይኽን ስለተቀበለም የሐዋርያትን ስብከት የሰሙትን ሰዎች ያሳድድ ነበረ። ሮማዊው ጲላጦስ ሊሰቅለው የሚችል መሢሕ ለእስራኤል ምን ክብር ሊያመጣ ይችላል? ስለዚኽ እነዚኽ ሰዎች እስራኤልን ሳያዋርዱ በፊት መጥፋት አለባቸው ብሎ ያምን ነበረ። በኋላ ግን፣ የትንሣኤው ጌታ አገኘውና “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለኽ?” ብሎ የገሊላዎቹ ዓሣ አጥማጆች የሚሰብኩት ነገር እውነት መኾኑን ዐወቀ። ሰማይ ምድሩ ዞረበት። ተሰቅሎ የተገደለው ኢየሱስ ለካ እውነትም ተነሥቷል። እስከዛሬ የነቢያትን መጽሐፍ ሲያነብብ የነበረው በተጠናገረ ዓይን ነበረ ለካ! ሰማይ ምድሩ ተገለባበጠ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንዳያይ ጋርዶ የያዘው ጨለማ ተገፈፈ። ነቢያትን እንደገና ተመለከታቸው። የእግዚአብሔር ትሕትና ተገለጠለት። መሢሑ ኤምፓየር ሊገነባ በጉልበትና በጦርነት ሳይኾን የእግዚአብሔርን መንግሥት በሰው ልብ ሊዘራ ሰው ኾኖ እንደመጣ፣ ሰዎች ግን ይኽን መረዳትም መቀበልም ስላልቻሉ ሰቅለው እንደገደሉት ገባው። በአዋራጁ የመስቀል ሥቃይ መሞቱም የእግዚአብሔር ንጹሕ ፍቅር በራስ ወዳድነት ላይ ከተመሠረተውና ከሚኖረው ኃጢኣተኛው የሰው ልጅ ጋር ሲገናኝ የሚፈጠር ተጠባቂ ውጤት መኾኑ ገባው። መስቀሉ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የወደደበት የፍቅሩ ጥግ ነው?! እግዚአብሔር ወትሮስ የጥላቻችንን፣ የክሕደታችንን መስቀል ተሸክሞ አይደል የሚኖረው? … ስለዚኽ፣ በአሕዛብ ከተማ ቆሮንቶስ ገብቶ የሰውን ልጅ ከማፍቀሩ የተነሣ እስከሞት ድረስ አብሮት የተዋረደውን የእግዚአብሔርን ልጅ ስቁል ኢየሱስን የዓለሙ ችግር ብቸኛው መፍትሔ፣ የእግዚአብሔር መሢሕ እንደኾነ ሰበከ። ይኽ የመስቀል መንገድ ግን የየራሳቸውን ኤምፓየር ለማቆም በተጠመዱት በአይሁድም በአሕዛብም ዘንድ እንግዳ ነበረ። 

ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መስቀሉ የምትሐት መሥሪያ ቁስ የሚመስላቸው ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ስለዚኽ እኛ እንግዲኽ ዓይኖቻችንን እንግለጥ። አባቶቻችን እንዳስተማሩን “ሀበነ እግዚኦ አዕይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ፤ ወአ እዛንነሂ ቃለ ዘባሕቲትከ ይስምዓ” (አቤቱ ዘወትር አንተን እናይ ዘንድ የሚያስተውሉ ዓይኖች ስጠን፤ ጆሮዎቻችንም የአንተን ቃል ብቻ ይስሙ!” እንበል። 

ጌታ ሆይ! ተሰቅለኽ ስናይኽ፣ በልጆች ውስጥ ዐቅመቢስ ኾነኽ፣ በድኾች ውስጥ ተርበኽ፣ በተጠሙት ውስጥ ተጠምተኽ፣ በታረዙት ውስጥ ታርዘኽ፣ በሕሙማን ውስጥ ታምመኽ፣ በዘመድ አልባዎች ውስጥ ብቸኛ ኾነኽ፣ “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውኸኝ?!” እያልኽ ስናይኽና ስንሰማኽ ኤምፓየራችንን በመገንባት ተጠምደን ፊታችንን ከአንተ እንዳናዞር፣ “መልክና ውበት የለውም፤ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም” ብለን ፊታችንን ገሸሽ እንዳናደርግብኽ ጌታ ሆይ! ልባችንን ለመስቀልኽ ክፈተው። ዓይኖቻችን አንተን ይዩ! ጆሮዎቻችንም አንተን ብቻ ይስሙ! አቤቱ፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ! በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለይም በምሥጢረ ቁርባን ከእኛ ጋር እንደኾንኽ በኑሯችን ኹሉ ከአንተ ጋር እንኹን። አሜን።

ልጁን ለሰጠን ለእግዚአብሔር አብ፣ ወደ አባቱ ላቀረበን ለእግዚአብሔር ወልድ፣ ቤተ ክርስቲያን በጸጋው ለሞላት ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምሥጋና ይኹንለት። ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለም። አሜን። 


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”