ንስሐ ግቡ

 “ኢየሱስ 'መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ።' እያለ ይሰብክ ጀመረ።” ማቴ. 4፡ 17

ንስሐ ግቡ! = μετανοεῖτε! = ዓላማን፣ ሐሳብን፣ አስተያየትን መቀየር

ይህ የጌታችን ስብከት ለአይሁድ መሰበኩ የሚገርም ነው። የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ፣ ርስቱ ነኝ ብሎ የሚያስብና ለሚመካ ሕዝብ “ንስሐ ግባ!” የሚል ድምፅ አስደንጋጭ ነው። ምን ያኽል ከእግዚአብሔር ርቆ እንደሚኖር ያሳያልና። እስራኤል እንዴት እዚኽ ደረሱ? 

  1. አስተሳሰባችኹን ቀይሩ!

ኢሳ. 55፡ 9 “ሐሳቤ እንደሐሳባችኹ፣ መንገዴም እንደመንገዳችኹ አይደለም” 

ንስሐ የኃጢኣት ሪፖርት አይደለም! 

ዓለምን፣ ሕይወትን፣ እውነትን የምናይበትን መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ማድረግ እንጂ። ለምን? 

አስተሳሰባችን ካልተቀየረ ኑዛዜ አይጠቅመንም። እግዚአብሔር የማያውቀው የኑሯችን ክፍል አለን? 

(ታዲያ የኑዛዜ ዓላማው ምንድነው? የኑዛዜ ዓላማው ከተሰለፍንበት ውጊያ እየከዳን የምንሸራተትበትን የኑሯችንን ስፍራ መለየት እንድንችል፣ ጉዟችን የውጊያ ነውና በውጊያው ላይ የሚያቆስሉንን የጠላት ፍላጻዎች በጥንቃቄ እንድንለይ፣ ዛሬ ያቆሰለን ነገ እንዳይገድለን እንድንጠነቀቅ፣ በኃጢኣት በመሰነካከላችን በሚመጣው የሰይጣን ክስ የተነሣ በብቸኝነት ተስፋ ቆርጠን እንዳንደርቅ፣ “እግዚአብሔር ይፍታሕ” በሚለው በካህኑ አንደበት ከቤተክርስቲያን የሚወርደውን የእግዚአብሔር ምሕረት እየጠጣን ለምልመን እንድንኖር ነው።)



  1. አስተያየታችኹን ቀይሩ!

“መሃይምነት የጨለማ ጉዞ ነው!” ይሉ ነበረ፣ መሃይምነት ምን ማለት እንደኾነ ያላወቁ የ1960ዎቹ “ምሁራን”። እንደርሱ ፎክረው ጀምረውም ማኅበረሰባቸውን ፊደል በፊደል አጥለቀለቁት ግን ፊደል ቋንቋ መጻፊያ ጥበብ እንጂ እንጂ ብርሃን አይደለም። የሰው ልጅም ጽሑፍ ስላላወቀ የጨለማ ኗሪ አይባልም። ማንበብና መጻፍ ማለት በጎ ማሰብና በጎ ማድረግ ማለት አይደለምና። በዓለም ታሪክ ከፍተኛው የጦርነት እልቂት የታየው አብዛኛው የሰው ልጅ ፊደል በቆጠረበት በ20ኛው ክፍለ ዘመን አይደለምን? ፊደል ዐዋቂዎች ሲበዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት በረከተሳ!? የተከረከመ የእጅ ጽሑፍ የተገረዘ ልብ አይወልድም። ታሪክ ጸሐፊዎች ስለበዙ ብቻ ከታሪኩ ያማረ ማኅበረሰብ አይፈጠርም። የጨለማ ጉዞ ፊደል አለማወቅ ሳይኾን ኃጢኣተኝነት ነው! ጥቁር መነጽር ያደረገ ሰው ኹሉ ጨልሞ እንዲታየው ኃጢኣተኛም ኹሉ ጨልሞ ይታየዋል። የዕውር ድንብር ይጓዛል። ከሌሎች ጋር ሲጋጭ ሲተራመስ፣ ሲያተራምስ ይኖራል፤ እይታው ጨልሟልና።  

አዳም ከእግዚአብሔር ጋር “ይኽች ሥጋ ከሥጋዬ ዐጥንቷም ከዐጥንቴ ነው”

አዳም ከሰይጣን ጋር “ይኽቺ የሰጠኸኝ ሴትዮ...!” 

ሌሎች ሰዎችን የማየው እንዴት ነው? ስለሌሎች ሰዎች የማስበውና የምናገረው ምንድነው? ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለኝ መስተጋብር የእኔ ድርጊት ምን ይመስላል? መንገዴ እንደ እግዚአብሔር ነው ወይስ እንደ ሰይጣን? ንስሓ?

  1. የኑሮ ዓላማችኹን ቀይሩ!

የመኖራችኹ ዓላማ ምንድነው? ሀብት? ሥልጣን? ዝና? ደስታ? ልጅ ማሳደግ? ገነት መግባት…?

Domine, non nisi Te.

በባግዳድ ጎዳናዎች ውኃና እሳት ይዛ የምትዞር አንዲት የጸሎት ሰው እንዲኽ ብላ ነበር፦ “ጌታ ሆይ! አንተን ለሚወድዱኽ ገነትን አውርሳቸው፤ አንተን ለማይወዱኽም የዚኽን ዓለም ክብርና ምቾት አልብሳቸው። ለእኔ ግን ከአንተ ከራስኽ ውጪ ምንም አልፈልግም።”

አባ ጊዮርጊስም በከባድ ሕመም ላይ ሳለ "ልትሞት ነው" ሲባል “አምላኬን አወድሼ ስላልጠገብኹ መኖር እፈልጋለኹ!” አለ። የኑሮ ዓላማው የገባው ክርስቲያን እንዲኽ ነው።



ንስሐ የገቡት ቀራጮችና አመንዝራዎች ሰው ኾኖ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ተቀበሉ። እኛም በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በተለይም ደግሞ ከኹሉ በበለጠ በቅዱስ ቁርባን በመካከላችን ያለውን የእግዚአብሔር መንግሥት ጌታችን ኢየሱስን እንድንቀበለው፣ ብርሃኑ ጨለማችንን እንዲገፍፍልን፣ ከእርሱ ጋር መኖር ዓላማችን እንዲኾን ዛሬ አስተያየታችንን እናስተካክል፤ የመኖራችን ምክንያት እግዚአብሔር ብቻ ይኹን፤ በምሥጢረ ጥምቀት ቃል የገባንበትን ለእግዚአብሔር የመኖር ዓላማ እናድስ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ እንግባ።

የማያልፍ መንግሥቱን በልጁ ለሰጠን ለእግዚአብሔር አብ፣ 

በቅዱስ ቁርባን የመንግሥቱን ማዕድ ላጠገበን ለእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ 

ቤተክርስቲያንን በምሥጢራት ጸጋ ላትረፈረፋት ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይኹን። 

አሜን


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”