ቤተ ክርስቲያንና ግለሰባዊነት

 የዕለቱ ግጻዌ ምንባቦች፦ ማቴ. 23፡23፣ ዕብ. 11፣ ራእ. 6፣9 እና ሐዋ 19፡1-6  እስመ ተዘከረ ዘይትኀሠሥ ደሞሙ መዝ 9፡17

“ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይኾኑ” ዕብ 11፡39

ዛሬ የዮሐንስ አባት ዘካርያስ እና የሙሴ መታሰቢያቸው ነው። ለምን ይታሰባሉ? ምክንያቱም በዘለዓለማዊው የሥላሴ ሕይወት ውስጥ ሕይወት ያገኘን አንድ ቤተሰብ፣ አንድ ቤተ ክርስቲያን ነን። 

  1. “ያለእኛ” = ቤተ ክርስቲያንና የሰው ልጅ የጋራ ዕጣ (ቤተ ክርስቲያንና ግለሰባዊነት) 

ነቢያቱ፣ በእምነት የተመሰከረላቸው፣ ስንት ድንቅና ተአምር የሠሩት፣ ስለ እርሱ ብለው መከራ የተቀበሉትን ያለ እኛ ፍጹማን አልኾኑም። ተስፋቸው የተፈጸመው፣ ትንቢታቸው የሠመረላቸው ቃል ሥጋ ሲኾን፣ የእግዚአብሔር አብ መንፈስ በልጁ በጌታ ኢየሱስ በኩል ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቶ፣ ሰዎች እግዚአብሔርን ዐውቀው፣ ወድደውና ተከትለው ሲኖሩ ነው። ቃል ሥጋ እስኪኾን፣ ቤተ ክርስቲያንም በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እስክትገለጥ ድረስ፣ እኛ እስክንመጣ ድረስ፣ ነቢያቱ እኛን ይጠብቁ ነበረ። 

እነሆ እኛም “ስለእግዚአብሔር የሚገደሉ የእግዚአብሔር ምስክሮች” ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ጌታችንን እንጠብቃለን። ለምን? ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር የሰውልጆችን በአምሳሉ ስለፈጠራቸው አንድ ሲኾኑ ብዙ፣ ብዙም ሲኾኑ አንድ ናቸውና። አንድ ሥጋ ናቸው። በኃጢኣት የተነሣ በዓለሙ ላይ ዛሬ ይኽ አይታይም፤ ሊታይም አይችልም። ሺሕ ጊዜ በመንደር ኾነ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በሺሕ ዓይነት መንገድ ሲደራጅ ቢኖርም በኃጢኣት የወደቀው ዓለም አንድ መኾን አልቻለም። ምክንያቱም የበሽተኞች መደራጀት ጤንነትን አይፈጥርም። 

በአንጻሩ፣ ቤተ ክርስቲያን ከዚኽ የሰው ልጅ እንደ ግለሰብም እንደማኅበረሰብም ተያይዞ ከሚዛቀጥበት የኃጢኣተኝነት ማጥ ውስጥ እንዲወጣ የምታደርገው፣ አንድ ሥጋ፣ አንድ ደም፣ አንድ መንፈስ ያላቸው ሰዎች ያሉባት ጉባኤ ናት። ይኽች ጉባኤ በዲያብሎስ ተንኮል ተሰናክለው፣ በኃጢኣት በሽታ ታምመው የተለያዩና እየተባሉ የሚኖሩትን የሰው ልጆች እግዚአብሔርን በማወቅ እንዲፈወሱ ለእውነት በፍቅር እያገለገለች፣ ለእውነት ምስክር እየኾነች ትኖራለች። የምትኖረው ለእነርሱ ነው። እነርሱም መንገዷ ከመንገዳቸው ጋር አብሮ ስለማይኼድ ዘወትር ይፈትኗታል፤ ጥበቧን ማሸነፍ ሲያቅታቸው። ይሰድቧታል፤ ይከሷታል፤ ይሰቅሏታል፤ ይገድሏታል። እርሷም እውነትን ሳያውቁ ከሚቀሩ በሞቷም ቢኾን እውነቱን እንዲረዱ ሞትን እንኳ ሳይቀር ያለማመንታት ትቀበላለች። ለምን? እርሷ ሥጋዋ ከሥጋቸው፣ ዐጥንቷም ከዐጥንታቸው እንደኾነ፣ የሥጋ ዘመዶቿ እንደኾኑ ታውቃለች። የሙሽራዋን ኑሮ ትኖረዋለች። ስለእርሷ እንደሞተ፣ ስለእነርሱ ትሞታለች። የሙሽራዋን ትንሣኤውን ትገልጣለች። ኑሮዋ ይኽ ነው። ከዚኽ ዓለም አምልጦ ገነት መግባት አይደለም፤ በውስጥዋ በሚመላለሰው፣ ሕያው ባደረጋት የሙሽራዋ ደም ዓለምን ማዳን እንጂ።      

  1. “ይገደሉ ዘንድ ያላቸው ባርያዎች” ራእ. 6፡ 11

ቤተ ክርስቲያን መኾን ማለት እንዲኽ መከራ ተቀብሎ የማዳን ሥራ መሳተፍ ስለኾነ፣ የቤተ ክርስቲያን ኑሮዋ መስቀል፣ ምልክቷም መስቀል ነው። ለምን ትኖሪያለሽ? ስትባል መልሷ “በክርስቶስ መከራ የጎደለውን ልሞላ” የሚል ነው (ቈላ. 1፡24)። ደግሞ በክርስቶስ መከራ ምን ይጎድላል? እኔ። እኔ ኃጢኣተኝነትን ትቼ ለእግዚአብሔር እስክኖር ድረስ የክርስቶስ ዓለሙን የማዳን ሥራው በእኔ ላይ አልተፈጸመም። ስለዚኽ፣ እያንዳንዱ ሰው ለእግዚአብሔር ካለመኖር አለመኖርን እስኪመርጥ ድረስ፣ የክርስቶስን መከራ እስኪሳተፍ ድረስ የክርስቶስ መከራ ስለእኔ ጎደሎ ይባላል። እርሱ ስላጎደለ ሳይኾን እኔ ስለጎደልኹ ነው። እርሱ ስለእኔ ይገደል ዘንድ እንደተገባው እኔ ስለእርሱ እገደል ዘንድ ሲገባኝ ያኔ ይሞላል።  

“እፎኑ ይከውን ዝንቱ?” (ይህ እንዴት ይኾናል?)

  1. “መንፈስ ቅዱስ”

በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ትምህርት ሰምተው ነበረ። የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀውም ነበረ። እናም ዐዲሱን የንስሐ ሕይወታቸውን፣ በዐዲስ ክርስቲያን ሚጢጢዬ ዕውቀትና ከሩቅ የሚፋጅ ቅንዓትና አርበኝነት ተሞልተው፣ በጉልበታቸው ሊወጡት ያሰቡ ይመስላል። 

ይኽን ዓይነቱን ኑሮ በተግባር የሚያውቀው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሲመጣ ክርስቲያኖቹ (ምናልባትም የራሱን ያለፈ የፈሪሳዊነት ሕይወቱን አስታውሰውት ይኾናል) አንድ የጎደላቸው ነገር እንዳለ አስተዋለ። ይኽ የጎደለ ነገር ካልተሟላ ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር እንደወቀሳቸው ወግ ጠባቂ ነን ባዮች፣ ግብዞች፣ አስመሳዮች፣ የይደረጋል አይደረግም፤ ይፈቀዳል አይፈቀድም ተጨቃጫቂዎች መኾን አይቀርም። በእንደዚኽ ዓይነት ሰዎች ዘንድ ጭካኔና ፍርድ እንጂ ምሕረትና ፍትሕ የሉም። ወግ ጠባቂነት፣ ትውፊት አስጠባቂ መባል ሕልማቸው ነው። ግን፣ በልባቸው ፍቅር የሌለ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው። ጳውሎስ ይኽቺን በኑሮው ያውቃታል። ስለዚኽ፣ ምን እንደ ጎደላቸው ገብቶታል። እናም ጠየቃቸው “ባመናችኹ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችኹን?”

ይኽ የጎደላቸው ዋና ነገር፣ መንፈስ ቅዱስ! ነበረ። ያለመንፈስ ቅዱስ ማፍቀር የለም፤ ያለ ፍቅርም እግዚአብሔርን ማወቅ የለም። “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም” (1ዮሐ. 4፡8) ተብሎ እንደተጻፈ። 

ዛሬ ይኽ ምሥጢር በምሥጢረ ሜሮን ይፈጸምልናል፤ የቤተክርስቲያን አገልግሎቷ ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ እንደኾነ እናምናለን። ታዲያ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ስለምን በየዐደባባዩ ማተብ አሥረው፣ መስቀል ጨብጠው የእገሌ ዘር የእንትን ዘር ሲሉ ይውላሉ? የክርስቲያን ቤተሰቦች ልጆች ምነው ከአሕዛብ ልጆች በምግባር አልለይ አሉ? ምናልባት ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ልማድ ኾነውብን ይኾን? በእነዚኽ ኹሉ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ እየበዛ ካልኼደን በራችንን ዘግተንበት ይኾን?             

ያለመንፈስ ቅዱስ ሰማዕትነት አይቻልም። ለሰማዕትነት የጨከነ ልብ ከሌለንም ሌሎችን መውደድ አንችልም። እነዚኽ ሦስቱ ግን የተሣሠሩ ናቸው። ስለዚኽ፣ ዛሬ የተለሰኑ መቃብሮችን እንዳንመስል በእግዚአብሔር ፊት እንንበርከክና ጌታ ሆይ! ለእኛ የሰማዕትነትን ሥራ ትሰጠን ዘንድ ሰማዕታት እንድንኾን እንማልዳለን ከሚለው የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ጋር ራሳችንን አንድ እናድርግ። 

ልጁን የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣ ወደ አባቱ ያቀረበን እግዚአብሔር ወልድ፣ ቤተ ክርስቲያንን በጸጋው የሞላት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምሥጋና ይድረሰው። አሜን። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”