“መንገዱ”

የዛሬ ምንባቦች፦ ሮሜ 1፡1-12፣ 1ኛ ጴጥ. 1፡ 13-22፣ ሐዋ 19፡ 1-11 መዝ 47፡7 ፣ ሉቃ 2፡ 36-42

መዝሙር፦ ተወልደ ኢየሱስ


የአስተንትኗችን መነሻ ሐዋ 19፡9 ላይ የሚገኘው “መንገዱ” የሚል ቃል ነው። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ በነበረበት ጊዜ ሲያስተምር አንዳንድ ሰዎች “እልኸኞች ኾነው በሕዝብ ፊት መንገዱን” እንደሰደቡ ይነግረናል። የጥንት ክርስቲያኖች “ራሳቸውን የመንገዱ ተከታዮች” ብለው ይጠሩ ነበረ። የኑሮ ዘይቤያቸውንም “መንገዱ” በግሪክ
ὁδὸσ ፣ በሱርስት ደግሞ ܐܘܪܚܐ ፣ በዕብራይስጥ הדרך እያሉ ይጠሩት ነበረ። ስለዚኽ መንገድ ሦስት ነጥቦችን እናንሳና ምንባቦቻችን ምን እያሉን እንደኾነ እንመልከት፦  

  1. በእምነት የመታዘዝ መንገድ 

ይኽ መንገድ ምን ዓይነት መንገድ ነው ብለን ስንጠይቅ መልሱን ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ “ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ” ሲል ይመልስልናል። የራሱን ማንነት ለሮሜ ክርስቲያኖች ሲያስተዋውቅም “በአሕዛብ ኹሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን” ይላል።  በሌላ አባባል፣ አሕዛብን ኹሉ አምነው እንዲታዘዙ ማድረግ የቤተክርስቲያን ቋሚ ሥራዋ እንጂ ሌሎች አካላት እስኪ የአካታችነት (inclusivity) ፖሊሲ ስለቀረጹ፣ ወይም እነእገሌ እነ እገሌንም ያካተተ የስብከት መርሐ ግብር አዘጋጂ ስላሏት አይደለም። ክርስቲያኖች የሚኖሩለትም፣ የሚኖሞቱለትም ሌላ ዓላማ የላቸውምና። በእምነት መታዘዝ መጀመሪያ እምነት ይጠይቃል። የሰው ልጅ በተፈጥሮው አማኝ ፍጥረት ነው። ዕውቀቱ ፍጹም ስላልኾነ ሳያምን መንቀሳቀስ አይችልም። ሌላው ቀርቶ በእግዚአብሔር አናምንም የሚሉ ሰዎች እንኳ አለማመናቸውን ባያምኑ ኖሮ የሚያደርጓቸውን ነገሮች አያደርጉም ነበረ። ይኽ እውነታ ግን ብቻውን የሰው ልጅ የሚያምነው ሊታመን የሚገባውን ነገር እንደኾነ ዋስትና አይሰጠንም። ስለዚኽም የሰውልጅ ብዙ ሊታመኑ የማይገባቸውን ነገሮች ሲያምን፣ ሲታመንና ሲተማመን እንመለከታለን። ለምሳሌ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴዎችን ኹሉ በዋናነት ከሚመሩ ስሑታን እምነቶች መካከል አንዱ “የሰው ሕይወት ዓላማው፣ ትርጉሙና ደስታው ምቾት ማግኘት ነው” የሚል ምቾት አምልኮ ነው። እነሆ አሕዛብና እንደአሕዛብ የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያኖች በዚኽ የምቾት አምልኮ ተጠምደው ሲባክኑ፣ ሲባትሉ፣ ሲናጩና ሲነጫነጩ ይኖራሉ። ቤተክርስቲያን እንዲኽ ዓይነቱን የነፍስ ዕረፍት፣ የኅሊናም ሰላም የማይሰጥ ከንቱ እምነትና ጣዖት አልምኮ አሽቀንጥራ ጥላ ሊታመን የሚገባውን፣ “በሥጋ ከዳዊት ዘር የተወለደውን፣ እንደቅድስና መንፈስም ከሙታን መነሣትን የተነሣውን የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚባለውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ትናገራለች። አዎን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ስም አለው፤ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ይባላል።

ቤተክርስቲያን ይኽን የተገለጠ ፍቅር ዘምራ አትጠግበውም። ስለዚኽም፣ “ተወልደ ኢየሱስ በቤተልሔም ዘይሁዳ። በተድላ መለኮት ተወልደ፤ ተጠምቀ፤ ወሠርዐ ሰንበተ ለዕረፍት ከመ ንትፈሣሕ በልደቱ ወንትሐሠይ በአስተርእዮቱ” “በይሁዳ ቤተልሔም ኢየሱስ ተወለደ። በመለኮት ደስታ ኢየሱስ ተወለደ። ተጠመቀ። በልደቱ ደስ እንዲለን፣ በመገለጡም ሐሤት እንድናደርግ ሰንበትን ለዕረፍት ሠራልን” እያለች ትዘምራለች።  ኑ ይኽን መገለጥ እመኑና ከመባከናችኹ ዕረፉ የሚል ጥሪ ነው። የሰው ልጆች እግዚአብሔር ምን ያኽል እንደወደደን፣ እንደሚወድደን ብናምን ልባችን በፍቅር ስለሚያዝ ለራስ ወዳድነት ስፍራ አይኖረውም ነበረ። ራስ ወዳድነት በሌለበት ግጭት፣ ጦርነት፣ ሽኩቻ፣ ሌብነት ከወዴት ይመጣሉ? ፍቅር የያዘውን ሰው ከፍቅር ውጪ ማን ያዝዘዋል? ከፍቅሩ ከሚፈልቀው በጎነት በስተቀርስ ሌላ ድርጊት ከወዴት ያመጣል? መንገዱ የፍቅር መንገድ ነው። 

  1. የልቡናን ወገብ መታጠቅ የሚጠይቅ የተስፋ መንገድ 

ይኽ የፍቅር ጉዞ የሚደረገው በዚኽ ራስ ወዳድነት ላይ በተመሠረተው የኃጢኣት ማኅበራዊ ሥርዓተ ዓለም ውስጥ ነውና ቀላል መንገድ ግን አይደለም። መንገዱ ለቆራጦች እንጂ ለልፍስፍሶችና ምቾት አምላኪዎች አይኾንም። ስለዚኽም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲኽ ሲል ይመክራል፦ “የልቡናችኹን ወገብ ታጥቃችኹና በመጠን ኖራችኹ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችኹ ተስፋ አድርጉ። … የጠራችኹ ቅዱስ እንደኾነ እናንተ ደግሞ በኑሯችኹ ኹሉ ቅዱሳን ኹኑ። ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችኹ ብትጠሩ በእንግድነታችኹ ዘመን በፍርኀት ኑሩ።” ለምን? እርሱ የሰጠውን የተስፋ ቃል አያጥፍማ! ይኽን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በተስፋ መጠባበቅ የሚለው ሐሳብ ምን እንደሚመስል ደግሞ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ነቢይት ሐናን ያሳየናል። ሐና ሰማኒያ አራት ዓመት ሙሉ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን በቤተመቅደሱ ትጠብቀው ነበረ። ሰማኒያ አራት ዓመት መጠበቅ! እውነት ነው፣ ለሙሴ የተገለጠውን እግዚአብሔርን በቤተመቅደሱ ሥርዓተ ጸሎትና ሥርዓተ መሥዋዕት እግዚአብሔርን በረድኤቱ ታገኘው ነበረ። ነገር ግን ከመገለጥ የሚበልጥ መገለጥ፣ ከመገኘትም የሚበልጥ መገኘት አለ። ይኽን የሚያውቀው ፍቅር የሚያውቅ ብቻ ነው። በደብዳቤና በስልክ፣ በኢሜይና በቻት ስታዋሩት የነበረን የምትወድዱትን ሰው ስታገኙ የሚሰማችኹን ልዩ ስሜት ታስታውሳላችኹ? ድንግልና ዮሴፍ ጌታን ይዘው ወደ ቤተመቅደስ ሲገቡ ነቢይቱ ሐና ናፍቆቷ ተሻረላት። ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የወሰነውን የእስራኤልን ተስፋ ከድንግል ዕቅፍ ውስጥ ሲያንቀላፋ፣ ድንግልም በእናትነት ፍቅርና ደስታ ስትስመው አየች። የነቢያት ተስፋ መፈጸሙ ገባት። “በከመ ሰማዕነ፤ ከማሁ ርኢነ” መዝሙሯ ኾነላት። ተስፋን የማያስቀር እግዚአብሔር ልቧን በደስታ መላው። ወገቡን ታጥቆ የሚጓዝ የፍቅር መንገደኛ ከግቡ መድረሱ አይቀርም፤ መጽሐፈ ምሳሌ “በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፤ ጌታውን የሚጠብቅ ይከብራል” እንዲል (ምሳ 27፡18)። መንገዱ የተዋህዶ የተገለጠውን፣ በቅዱስ ቁርባን ከቤተክርስቲያኑ ጋር የሚኖረውን ዳግመኛም የሚመጣውን ጌታ ኢየሱስን የምንጠብቅበት የተስፋ መንገድ ነው።  

  1. መገልበጥ የሌለበት መንገድ 

እንግዲኽ ይኽ መንገድ አደጋ አያሰጋውም፤ መገልበጥ የለበትም። ከዚኽ መንገድ ውጪ ያሉት ሌሎች መንገዶች ኹሉ መንገዶች አይደሉም። ወደ ዕረፍታችንም አያደርሱም። ይልቁንም በጥቂት ጊዜ ውስጥ እኛንም፣ ገነባነው ያልነውንም በራስ ወዳድነት ፖሊሲ የተሠራ የሀብት፣ የዝና፣ የሥልጣንና የምቾት ግንብ ይዞት ይገለበጣል።  የነነዌ ሰዎች የኾኑ እንዲኽ ነው። የሦስት ቀን መንገድ ስፋት ያላት ዝነኛ፣ ሀብታም፣ ባለሥልጣኖች የበዙባት ምቹ ከተማ ገነቡ። ግን መሠረቷ እግዚአብሔር አይደለምና የገነቡት ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ የሚውጥበት ሥርዓት “ሊገለበጥ” ጫፍ ደረሰ። ዮናስ “ነነዌ በሦስት ቀን ትገለበጣለች!” ሲላቸው እጅ ሰጡ። ከመገልበጥም ተረፉ። ቤተክርስቲያን ይኽንን ጾም እንድንጾም ስታዝዘን በእምነት የመታዘዝ ኑሯችንን ዘወር ብለን እንድንፈትሸው እየጋበዘችን ነው። ከምግብ ብቻ ሳይኾን ከወሬ ጾመን በጽሙና ራሳችንን በምሥጢረ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ጋር ለመሠረትነው ትዳር ታማኝ መኾን አለመኾናችንን እንድናይ፣ በመንገዱ ላይ እየኼድን መኾን አለመኾኑን እንድናስተውል፣ በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በተለይም ደግሞ በቅዱስ ቁርባን አብሮን ከሚኖረው፣ መንገዳችን ከኾነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መኾን አለመኾናችንን የምንገመግምበት ወቅት ነው። ካልኾንንም የኑሮ መንገዳችንን አስተካክለን ወደ መንገዱ ወድ ኢየሱስ ክርስቶስ “ኪርዬ ኤሌይሶን!” ብለን የምንመለስበት ጊዜ ነው። 


ልጁን መንገድ አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር አብ፣ መንገዳችን የኾነልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመንገዱ ላይ የሚያጸናን ቤተክርስቲያንን በጸጋው የመላት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምሥጋና ይኹንለት። አሜን።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

“ዓለም በልጁ እንዲድን እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ 3፡17)

“ወደ ሠርግ ገቡ።” (ማቴ 25 ፣ 10)

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን።”