ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው! ኤፌ 5፡ 32
“ዐቢይ ውእቱ ዝ ነገር!”/ “ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው!”/ “τὸ μυστήριον τοῦτο μέγα ἐστίν” ኤፌ 5፡ 32
የትኛው? ሦስት ነጥቦችን ላንሣ፦
እግዚአብሔር ፍጥረትን የወደደበት ዘለዓለማዊ ምሥጢር
ከልግስናው፣ ከደግነቱ፣ ከአፍቃሪነቱ ብዛት ህልውና ያልነበረውን ዓለም ካለመኖር ወደመኖር አመጣው፤ ፍጥረትን ኹሉ ወክሎ ሲጠራ አቤት ብሎ ለተወደደበት ፍቅር ምላሽ መስጠት የሚችል የሰውን ልጅም በፍጥረቱ ላይ ጉልላት አድርጎ አኖረ። ይኽን ያደረገበት ምክንያትም የፍጥረት ራስ የኾነው የሰው ልጅ እግዚአብሔር ፍጥረትን ለወደደበት ዘለዓለማዊ ፍቅር የፍቅር ምላሽ በመስጠት ከእርሱ ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር አንድ አንድ ኾኖ እንዲኖር ነው። በዚኽ አንድ በኾነበት ፍቅርም የእግዚአብሔር ብቻ የኾነው ሕያውነት ኹሉ የሰው ልጅ ሀብት ይኾናል። ክብሩን ይለብሳል። ሕይወቱን ይወርሳል። ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስለኾነ ከዐፈር የተበጀው፣ ህልውና፣ ሕያውነት የሌለው የሰው ልጅ ሕያው፣ ህልው ይባላል። ሕያው ኾኖም ፍጥረትን ኹሉ ሕያው ያደርጋል። ራሱ ሕያው ከኾነ አካሉም ሕያው ነውና። ይኽ ከእግዚአብሔር ለፍጥረት የተለገሰ ፍቅር ፍጹም ስለኾነ ከሰው ልጅ የሚገኘው ምላሽ ምንም ቢኾን አይለወጥም። በዚኽ ዘመነ አስተርእዮ በቤተ ክርስቲያን የምናስበው፣ የምናመልከውም ይኽንን ዓለም ሳይፈጠር በፊት ጀምሮ የተወደድንበትና ዘመኑ በደረሰ ጊዜ በእግዚአብሔር ልጅ ሰው መኾን የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው። ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ ለእኛ የነበረው እኛ የእርሱ ኾነን፣ እርሱም የእኛ ኾኖ የመኖሩን ዕቅድ ፈጸመው። ብንበድለው ይቅር ብሎ፣ ብንርቀው ቀርቦ የፍቅሩን ዕቅድ ፈጸመው። ዳግም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ነፋስ እንዳይገባ፣ መተጣጣት እንዳይኖር በተዋህዶ አንድ ኾነ። ኃጢኣት እኛን ኾነ፣ ከድንግል ተወልዶ፣ ኃጢኣት የሌለበት እርሱ ለንስሐ ከሚጠመቁ ኃጢኣተኞች ተርታ እስከመሰለፍ ድረስ ወርዶ ራሱን ከእኛ ጋር አንድ አደረገ። ዕድል ፈንታችንን፣ ጽዋ ተርታችንን የራሱ አደረገው። የሊዮኑ ጳጳስ ቅዱስ ሔሬኔዎስ ከዛሬ 1800 ዓመታት ገደማ በፊት እንዳለው “የሰው ልጅ አምላክ ይኾን ዘንድ፤ አምላክ ሰው ኾነ።” በተዋህዶ ምሥጢር ፍጥረት ለእግዚአብሔር ተዳረች። እግዚአብሔር አብ ልጁን በማይፈርስ ትዳር ለፍጥረት ዳረው። አምላክ ሰው ኾነ፤ ሰው አምላክ ኾነ። ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው!
የጋብቻ ምሥጢር
እንግዲኽ ክርስቲያን ትዳር ሲመሠርት ይኽን የእግዚአብሔርንና የፍጥረትን፣ የኢየሱስ ክርስቶስንና የቤተክርስቲያንን ፍቅር ሊኖረው እየፈቀደ ነው። ስለዚኽም ምሥጢር ይባላል። በምናያቸው ሙሽራና ሙሽሪት፣ አንዳቸው ለሌላቸው ባላቸው በየዕለቱ ወደ ፍጽምና የሚያድግ ፍቅር የክርስቶስና የቤተክርስቲያንን እስከሞት ድረስ የደረሰ ፍቅር እናያለን። እንዳስሳለን። እግዚአብሔር በእነርሱ ተገልጦ ይኖራል። በሚታዩት ባለትዳሮች የማይታየው የክርስቶስና የቤተክርስቲያን ፍቅር ተገልጦ ይገኛል። ስለዚኽም ምሥጢር ተባለ።
ተጋቢዎቹ ሙሽራው ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ባፈቀረበት ልክ ሚስቱን እስከሞት ድረስ ለማፍቀር፣ ሙሽሪትም ቤተክርስቲያን ክርስቶስን እስከ ሰማዕትነት ድረስ እንደወደደችው ለመውደድ ቃል ገብተዋል። እኛም ከዚኽ በኋላ አንዳቸው ለሌላቸው በመኖር የፍቅር ሰማዕታት እንዲኾኑ በኦርቶዶክሳዊት ሥርዓተ አምልኮ መሠረት የሰማዕታትን አክሊል ምሳሌ በራሳቸው ላይ አኑረናል። አንዳቸው ሌላቸውን በፍጹም መሰጠት እንዲያገለግሉም መላ ሰውነታቸውን የሚሸፍን ካባን ደርበንላቸዋል። የተዋህዷቸውንም ፍጽምና ለማመልከት ፍጹም ክብ የኾኑ ቀለበቶችን “ይኩኖሙ ትእምርተ ማእሠረ ተዋህዶ!” (ለአንድነታቸው ማሠሪያ ምልክት ይኹናቸው!) ብለን ሰጥተናቸዋል። እንዲኽ ብለንም ጸልየናል፦ “ከመ ይኩኑ ድልዋነ ለአርኣያ ትእምርተ ቃልከ በማእሠረ ዐረቦን ከመ ይኩን ሎሙ ፍቅር ዘኢይትፈለጥ በበይናቲሆሙ በጻዕቅ ጽኑዕ ላዕለ መሠረተ ቤተ ክርስቲያን” (በዐረቦኑ (በመንፈስ ቅዱስ) ማሠሪያ ለቃልኽ አርኣያነት ምልክት የተዘጋጁ እንዲኾኑ በመካከላቸው የማይለያይ ፍቅር ይኾንላቸው ዘንድ፤ ይኸውም በቤተክርስቲያን ላይ የተመሠረተውና የጠበቀው ፍቅር ነው።) (That they may become worthy of the example of the sign of Thy Word, by the bond of the gift of the Holy Spirit, that there may be between them indivisible love established upon the foundation of the Church;)
ይኽ ምን ዓይነት ፍቅር ነው? ለጋስ የኾነ ፍቅር ነው። መቀበልን ሳያሰላ የሚሰጥ ፍቅር ነው። ዕረፍትን ሳይሻ የሚለፋ፣ ሽልማትን ሳይፈልግ የሚተጋ፣ በየዕለቱ ምቾቴን እንዴት ላደላድል ሳይኾን “ዛሬ እግዚአብሔርን በሙሽራዬ ውስጥ እንዴት ላገልግለው?” ብሎ የሚጠይቅ ፍቅር ነው። እውነት ነው። ይኽ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እግዚአብሔር ወልድንና አካሉን ቤተክርስቲያንን መስሎ፣ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ኾኖ የመኖር ምሥጢር እጅግ ታላቅ ነው።
የፍቅር ፍጻሜ
ዛሬ የእመቤታችን ዕረፍቷ የሚታሰብበት ዕለት ነው። ቤተ ክርስቲያን እመቤታችንን ልደቷንም ኾነ ዕረፍቷን የምታስብበት ዐቢይ ምክንያቶች ኹለት ናቸው። አንደኛው፣ ምክንያት ቃል ሥጋ ለመኾኑ ማረጋገጫ ስለኾነች ነው። እመቤታችን ሰው ናት። ስለዚኽም የእርሷን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን “ሰው አይደለም! ምትሐት ነው! ሚቶሎጂ ነው!” ብሎ መከራከር አይቻልም። ኹለተኛ፣ የእመቤታችን ሕይወት ቤተክርስቲያን የተጠራችለትን የፍቅር ጥሪ፣ የመስቀል ጉዞ እና ዘለዓለማዊ መድረሻ ያሳያል። ድንግል ማርያም ጥሪዋ መሢሑን ወልዳ ለዓለም መስጠት ነበረ፤ ቤተ ክርስቲያንም ጥሪዋ መሢሑን ሙሽራዋን ጌታ ኢየሱስን አጥቶ በኃጢኣት ጨለማ ለሚደናበረው ዓለም መስጠት ነው። ድንግል የጌታ እናት በመኾኗ ስደት መከራ፣ የእብድ እናት መባል፣ ንጹሕ ልጇ ያለ በደሉ በአሰቃቂው የመስቀል ሥቃይ ኣይኖቿ እያዩ ሲገደል የማየት መከራ ደርሶባታል። ዓለም በሚገፋው የልጇ ፍቅር የተነሣ ልቧ ሲደማ ኖሯል። ቤተክርስቲያንም ሙሽራዋን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ስለምታቀርብ፣ በእርሱ የፍቅር መንገድ ብቻ ስለምትኼድ፣ የዓለምን ራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ትታ ለእግዚአብሔር ፍቅር ስለምትኖር እንደሞኝ፣ እንደ ማኅበረ ደናቁርት ስትቆጠር፣ ስትሰደብ፣ ሲብስም ስትሳደድ ትኖራለች። እርሷ ግን የሙሽራዋ ፍቅር የልቧ መልሕቅ ኾኖላት ዓይኖቿን ከእርሱ ሳታነሣ ትኖራለች። ልቧ በሙሽራዋ ፍቅር ሐሴት ያደርጋል፤ ዓይኖቿም ከመከራዋ የተነሣ በሚፈልቀው የሚያቃጥል እንባ የተመሉ ናቸው። ኑሮዋ ፍቅርና እንባ የተቀላቀለበት ኑሮ ነው። መልካሙ ዜና፣ መከራው እስከሞት ድረስ ብቻ ሲኾን ፍቅሩ ግን የመቃብር ድንጋይ እንኳ አያሸንፈውም። የድንግል ሞቷ ለምእመናን ኹሉ በተሰጠው በልጇ የትንሣኤ ሕይወት ውስጥ ስለኾነ ዕረፍታ ለማርያም፣ ፍልሰታ ለማርያም እንደሚባል፣ የቤተክርስቲያን (የክርስቲያኖች) ፍጻሜም በወደደን፣ በምሥጢረ ቁርባን ሥጋውን በልታ ደሙን ጠጥታ አካሉ እንድትኾን ወዳደረጋት፣ የትንሣኤው ጌታ ሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚኽ፣ የክርስቲያን ሞቱ የሕይወቱ አንድ ምዕራፍ አክትሞ ሌላ ምዕራፍ መከፈት እንጂ የኹሉ ነገር ፍጻሜ አይደለም። እዚኽ በፍቅር አብረን የኖርነው ጌታ ከሞት በኋላም በፍቅሩ ሕያዋን ኾነን እንኖራለን። በዘመን ፍጻሜም በሞት የተለየነውን ሥጋችንን በትንሣኤ ከብሮና በሕይወት ተመልቶ መልሰን እንቀበለዋለን። እውነት ነው፣ ሞትን የረታንበት ይኽ በምሥጢረ ሜሮን ስንከብር “በልባችንን የፈሰሰው” የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፍቅር፣ ሞትን ያሸነፍንበት ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው። “τὸ μυστήριον τοῦτο μέγα ἐστίν”!
በዘለዓለማዊ ፍቅሩ የወደደን፣ አንድ ልጁን ለቤተ ክርስቲያን ሙሽራ አድርጎ የሰጠን፣
ቤተክርስቲያንንም በሕያው መንፈሱ ጸጋ የሞላት
ልዑል እግዚአብሔር አብ ክብር ምሥጋና ይኹንለት።
አሜን።
ቅድስት ሆይ ለምኚልን!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ