መብዛት፣ መጾም እና መቀደስ
“ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን።” ኤፌ 4፡ 11 “ περισσεύητε” ፩ ተሰ ም. ፬፥ ቍ. ፩-፲፫ ፤ ፩ ጴጥ፡ ም. ፩፥ ቍ. ፲፫-ፍ፡ም ፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፲፥ ቍ. ፲፯-፴ ፤ መዝሙር፡ ፺፭(፺፮)፥ ቍ. ፭-፮። ማቴዎስ፡ ም. ፮፥ ቍ. ፲፯-፳፭ የዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት ላይ ነን። ሳምንቱ ቅድስት ይባላል። ከዚኽ ሳምንት ጀምሮ እስከ ሆሳዕና ድረስ ያለው ጊዜ "ጾመ አርብዐ"፣ "ጾመ ኢየሱስ" ይባላል። ለዚኽ እሑድ የተመደቡት ምንባቦች ኹሉም ቅድስና ምን እንደኾነ፣ ለሰው ልጅ ምን ያኽል አስፈላጊ እንደኾነና የቅዱስ ሰው ኑሮም ምን መልክ እንዳለው ይናገራሉ። መዝሙረኛው “ምሥጋናና ውበት ሰማያትን በሠራው በእግዚአብሔር ፊት፣ ቅድስናና ግርማም በመቅደሱ ውስጥ እንደኾኑ” ይዘምራል። ጌታ ኢየሱስም “ስትጾሙ እንደግብዞች አትኹኑ!” እያለ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጾም ምን እንደሚመስል ያስተምራል። ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ፈቃድ የእናንተ መቀደስ ነው” ይላል። ቅዱስ ጴጥሮስ “በኑሯችኹ ኹሉ ቅዱሳን ኹኑ” ይላል። የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊው ቅዱስ ሉቃስም በምጽዋቱና በጸሎቱ የሚታወቀው መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ቅድስናው ይጨምር ዘንድ ጴጥሮስን 40 ማይል ገደማ ርቃ ከምትገኘው ከኢዮጴ ልኮ ሲያስመጣ ሰምተናል። ጾመ ድጓውም “ሰንበትየ ቅድስትየ” እያለ ሰንበትን ከማሞካሸት በተጨማሪ “ተፋቀሩ፡ በምልዓ፡ ልብክሙ። አክብሩ፡ ሰንበተ፡ በጽድቅ፡ ዝግቡ፡ ለክሙ፡ መዝገበ፡ ዘበሰማያት፡ ኀበ፡ ኢይበሊ፡ ወኢይማስን” (በፍጹም ልባችኹ ተፋቀሩ። ሰንበትን በጽድቅ አክብሩ። በሰማያትም ብል የማይበላውና የማይጠፋ ሀብትንን ሀብትን አከማቹ) እያለ እነዚኽኑ ምንባቦች ይዘምራል። እነዚኽን ኹሉ ምንባቦች መብዛት፣ መጾም እና መቀደስ በሚሉ ሦ...