ትንሣኤ ስም እና ቅድስና
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን! በአማን ተንሥአ! የዕለቱ ምንባቦች፦ ፩ኛ፡ ቆሮ፡ ም. ፲፭፥ ቊ. ፩-፳፤ ፩ኛ፡ ዮሐ፡ ም. ፩፥ቊ. ፩-ፍ፡ም፤ ግብ፡ ሐዋ፡ ም. ፳፫፥ ቊ. ፩-፲፤ ዮሐንስ፡ ም. ፳፥ቊ. ፲፱-ፍ፡ም፤ ዮሐንስ፡ ም. ፲፯፥ ቍ. ፩-ፍ፡ም። ትንሣኤ የበዓላት ኹሉ በኵር፣ የቤተክርስቲያን ትርጉምና ድሏ የሙሽራዋ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው። ስለዚኽም፣ ከበዓላት ኹሉ ከፍ አድርጋ ትንሣኤን ታከብራለች። በክርስቶስ ትንሣኤ ውስጥ ያለውን ደስታ፣ ተስፋና ሕይወት በሚገባ እንድናጣጥመውም ስምንት ቀናትን እንደ አንድ ቀን ቆጥራ ስታከብር፣ እርሱም አልበቃ ብሎ እስከ ዕርገት በዓል ድረስ ያሉትን 40 ቀናት ስትጨምርበት እናያታለን። ለምን? ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት ካልኾነ ቤተክርስቲያን ከንቱ ናት። የነቢያት ትንቢት፣ የሐዋርያትም ስብከት፣ የሰማዕታት መከራ፣ የእናንተም ጾምና ጸሎት የመቃብር ድንጋይ ደፍጥጦ በዜሮ የሚያባዛው ከንቱነት ይኾናል። ሰው ኾኖ መኖርም ትርጉም የሌለው የመከራ ቀንበር ይኾናል። ግን ክርስቶስ በእውነት ከሙታን ተነሥቷል ስለዚኽም ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው፣ “ በኹሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ኹልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። ” (2ኛ ቆሮ. 4፡8) ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይለናል! (ፊል 4፡4) ስም ይኽ ዛሬ ከዮሐንስ ወንጌል የተነበበው ምንባብ የጌታ ኢየሱስ የሊቀ ካህንነቱ ( כהן גדול) ( ἀρχιερεύς) ጸሎት ይባላል። ከዚኽ ጸሎት ቀጥሎ የሚመጣው የዓለሙን ኃጢኣት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ ...