ልጥፎች

ከሜይ, 2023 ልጥፎች በማሳየት ላይ

“የለንም!”

ምስል
ምንባባት፦ ሮሜ ፬፥ ቊ. ፲፬-ፍ፡ም፤ ራእ ፳፥ ፩-ፍ፡ም ፤ ሐዋ ፲፥ ፴፱-፵፬ ፤ መዝ ፸፯(፸፰)፥ ፳፱-፴ ፤ ዮሐ ፳፩፥ ፩-፲፭ ።   የዛሬው ወንጌል ቢያንስ ሦስት መሠረታዊ የክርስትና ምሥጢሮችን ይነግረናል።  ትንሣኤና ፍቅር   በዛሬው ወንጌል ውስጥ ከምናያቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ሥልጣኑን፣ ወይም ትክክለኛነቱን ለማሳየት ከሃይማኖት ተቋማቸው የሚያገኙትን ጥቅም፣ ክብርና ምቾት ለማስጠበቅ ሲሉ ወደገደሉት ካህናትና መምህራን ወይም ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል በግፍ እንዲሰቀል አሳልፎ ወደ ሰጠው ወደ ጲላጦስ ሥልጣኑን ሊያሳያቸው፣ እውነተኛ መሢሕነቱን እግዚአብሔር ከሞት በማስነሣት እንደገለጠ በመመስከር ሊያሳፍራቸው አልኼደም። “እኔ ትክክል ነበርኹ እናንተ ግን ስሕተተኞች፣ ወንጀለኞች ናችኹ” አላላቸውም። ክብሬ ተነካ የምትል አተካራ በእርሱ ዘንድ የለችም። ምክንያቱም እርሱ የሰው ክብር አይፈልግም (ዮሐ 5፡ 42)። ይልቁንም ወደሚወድዱት፣ ወደሚናፍቁት፣ እርሱን በማጣታቸው ሕይወታቸው ወደ ተመሰቃቀለባቸው፣ የትንሣኤውን ዜና ሲሰሙ ደግሞ ግራ ወደ ተጋቡት ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። የዛሬው ወንጌል የሚነግረን ጌታ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጠላቸው ነው። እስከሞት ድረስ የወደዳቸውን ወዳጆቹን ከትንሣኤው በኋላም “በቃ፣ ሥራዬን ጨረስኹ!” የራሳችኹ ጉዳይ ብሎ ጥሏቸው አልኼደም። በፍርኀት ቤት ዘግተው ሲቀመጡ የተዘጋ ቤት ውስጥ ገብቶ፣ ጥርጥር በልባቸው ሲሰፍን እጆቼንና እግሮቼን ዳስሱኝ ብሎ፣ ትንሣኤውን በማመን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን የዘለዓለም ተስፋ ላይ ልባቸውን እንዲያሳርፉ ደጋግሞ ታይቷቸዋል። ዛሬ እንደተነበበልን ደግሞ ኹልጊዜም ከእነርሱ ጋር እንደኾነ፣ ድካማቸውን እንደሚያ...